Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ስምምነቱን ለማፅናትና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ጉዞ ለማሳካት ዝግጁ ነን-የትግራይ ክልል ምሁራንና ወጣቶች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ስምምነቱን ለማፅናትና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ጉዞ ለማሳካት የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የትግራይ ክልል ምሁራንና ወጣቶች ገለጹ።

የትግራይ ክልል ተወላጅ ምሁራንና ወጣቶች በኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ፣ በሰላም ስምምነት አተገባበር፣ በትግራይ ክልል መልሶ ግንባታና የሀገርን ልማት በማረጋገጥ ሂደት የሚኖራቸው ሚና ላይ ምክክር አድርገዋል።

በምክክሩ መንግስት በሀገራዊ ለውጡ ያከናወናቸውን ተግባራትና አሁን የሰላም ስምምነቱን በማስፈጸም ረገድ ያለውን ቁርጠኝነት በተመለከተ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጂጌ እና በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ዛዲግ አብርሃ ገለጻ አድርገዋል።

በዚህም መንግስት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ከመሰረታቸው ለማስወገድ የሪፎርም ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

ሆኖም በለውጡ ሂደት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች መፈጠራቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

መንግስት ጦርነቱ ከመከሰቱ በፊት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ በተግባር ያሳየ መሆኑን አስታውሰው፤ ጦርነቱ ከተከሰተ በኋላም ቢሆን ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መስራቱን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግስት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ያለምንም መዛነፍ እየተገበረ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው÷ መንግስት በሀገሪቱ ልማትንና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው የሰላም ስምምነቱ ለትግራይ ህዝብ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የትግራይ ህዝብ ከዚህ በኋላ ጦርነት የሚሸከምበት ትከሻ የለውም ያሉት የውይይት ተሳታፊዎች፤ የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም ለሰላም ዘብ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ የክልሉን ተወላጆች በማስተባበርና የተገኘውን ሰላም በማፅናት ረገድ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.