Fana: At a Speed of Life!

በህገወጥ መንገድ ተፈትቶ ሲዘዋወር የነበረ ከ2 ሺህ 500 በላይ የባቡር ሃዲድ ማቀፊያ ብሎን ተያዘ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገወጥ መንገድ ተፈትቶ ሲዘዋወር የነበረ 2 ሺህ 590 የባቡር ሃዲድ ማቀፊያ ብሎን በሶማሌ ክልል ኤረር ወረዳ መጋሌ አድ ቀበሌ ከነተጠርጣሪዎቹ ተያዘ፡፡

የባቡር ሃዲድ ማቀፊያ ብሎን ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልል የፀጥታ አካላት ባደረጉት ከፍተኛ ኦፕሬሽን መያዙን የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር አስታውቋል፡፡

በወንጀሉ የተሳተፉ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም የማህበሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ አብዲ ዘነበ÷በስፍራው በመገኘት የፌዴራልና የክልል ፀጥታ አካላት ከህብረተሱ ጋር በመቀናጀት የባቡር መሰረተ ልማት ደህንነቱን ለማስጠበቅ እያደረጉት ላለው ጥረት አመስግነዋል፡፡

ከፌዴራል ፖሊስና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የመስመሩን ደህንነት የመጠበቅና የማረጋገጥ ስራ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ ከዚህ ቀደም በመስመሩ ይደርሱ የነበሩ ችግሮች በሂደት እየቀነሱ መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡

በተደጋጋሚ በሚደረጉ ፍተሻዎችም የተዘረፉ መሰረተ ልማቶችና ወንጀለኞቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸው በቅንጅት የመስራት ትልቅ ውጤት በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራሩ ይበልጥ ይጠናከራል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.