Fana: At a Speed of Life!

የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ ባለው እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ መሆን ይገባል – አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም በማረጋገጥ ባለው እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ መሆን ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ ትጥቃቸውን ፈትተው በሰላም ወደ ክልሉ ለገቡት የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) አባላት የክልሉን ፖለቲካዊ መዋቅርና ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ስልጠና እና ገለጻ ሰጥተዋል።

አባላቱ ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ክልሉ ከገቡ በኋላ በህገ መንግስትና የሰላም ግንባታ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ለህዝቦች መብት የሚታገሉ እስከሆነ ድረስ በሰላም የመታገል መብታቸው የተከበረ ነው ብለዋል አቶ አሻድሊ፡፡

ሆኖም ግን በተለያዩ ምክንያቶች የትጥቅ ትግል መርጠው ወደ ጫካ በገቡ ቡድኖች ምክንያት ለረጅም ጊዜ ክልሉ የሰላም እጦት እንዳጋጠመው አንስተዋል።

በዚህም በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን እንዳጡና ሃብት ንብረታቸው እንደወደመም ነው የተናገሩት።

የክልሉ መስተዳድር ለረጅም ጊዜ የጠፋውን ሰላም ለመመለስ የትጥቅ ትግል ከሚያደርጉ ቡድኖች ጋር በመነጋገር ችግሮችን በሰላም በመፍታት አብሮ ለመስራት መወሰኑን አረጋግጠዋል፡፡

የክልሉን ሰላም በመመለስም ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም በጋራ ለልማት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የተሃድሶ ስልጠናውን እየወሰዱ የሚገኙት የቤህነን አባላትም ፥ እስካሁን በትጥቅ ትግል ውስጥ በመቆየታቸው እንታገልለታለን ያሉት ህዝብ የባሰ ችግር ውስጥ እንዳስገቡት ተናግረዋል።

አሁን ግን ህዝቡ ካጋጠመው ተደራራቢ ችግር እንዲወጣ በሰላማዊ መንገድ ከመንግስት ጋር አብሮ በመሆን ለክልሉ እድገት እንደሚሰሩም አንስተዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.