Fana: At a Speed of Life!

የእምቦጭ አረምን ከጣና ሃይቅ በዘላቂነት ለማስወገድ የክልልና ፌዴራል መንግስታት ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጣና ሃይቅ የእምቦጭ አረምን በዘላቂነት ለማስወገድ የክልል እና የፌዴራል መንግስታት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የጣና ሃይቅ እና የሌሎች ውሃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ባለፉት ዓመታት በጣና ሃይቅ ላይ የተሰራጨውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በዚህ መሰረትም በቴክኖሎጂ ማሽን እና በሰው ሃይል ጉልበት አረሙን ከሃይቁ ለመንቀል በተካሄደ ዘመቻ አበረታች ስራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ የቅንጅት ስራም ህብረተሰቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቁርጠኝነት ከሰራ አረሙን ከሃይቁ ለማስወገድ እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በክልሉ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የእምቦጭ አረምን ከጣና ሃይቅ ለማስወገድ የሚደረገው ርብርብ መቀዛቀዙን ነው የተናገሩት፡፡

አሁን ላይ 2 ሺህ ሄክታር በላይ የጣና ሃይቅ በእንቦጭ አረም መሸፈኑን ጠቁመው÷ አረሙን በዘላቂነት ለማስወገድ ከአንድ ወቅት ዘመቻ ይልቅ በስትራቴጂያዊ እቅድ መመራት ይገባል ብለዋል፡፡

አረሙን ለመንቀል የአካባቢውን ህብረተሰብ ግንዛቤ በመፍጠር እና ማበረታቻ በመስጠት የተጀመረው ስራ ከክልሉ ብሎም ከፌዴራል መንግስት ድጋፍ ባለመኖሩ ውጤታማ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዳያስፖራው በድጋፍ የመጡ ማሽኖችም የሃይቁን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ባለመሆናቸው የተጠበቀውን ያህል እየተሰራባቸው እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡

በቀጣይ በሃይቁ ዳርቻ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ንቅናቄ መልክ ግንዛቤ በመፍጠርና ማበረታች በመስጠት በአዲስ መልክ ስራውን ለማስጀመር ስትራቴጂ መነደፉን አንስተዋል፡፡

ለዚህም ህብረተሰቡ ዓረሙን ለመንቀል የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች እና ማበረታቻዎች ለማቅረብ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው እግዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ተቋማት ሃይቁ ለሀገር ያለውን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት እቅድ ይዘው እና ቋሚ በጀት በመመደብ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከዚህ ባለፈም አረሙ በነበረበት ቦታ ነባር እጽዋቶችን በመትከል እና እንዲያገግሙ በማድረግ ስነ ምህዳሩን መጠበቅ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.