Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ የምግብና የሥርዓተ-ምግብ ደኅንነትና ዋሥትና እየተሻሻለ መጥቷል – አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ የምግብና የሥርዓተ-ምግብ ደኅንነትና ዋሥትና እየተሻሻለ መምጣቱን የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ፡፡

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለዕመርታው መመዝገብ የሚመለታቸው የሥራ ኃላፊዎች ርብርብ እንዲሁም የሀገራት መሪዎች ቁርጠኛ ውሳኔ እና የሚያፈሱት መዋለ ንዋይ አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን አመላክተዋል፡፡

የ”ግሎባል አልያንስ” ተቋም በኢትዮጵያ የ10ኛ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት አክብሯል፡፡

ተቋሙ በምግብና ሥርዓተ-ምግብ ላይ ሲሰራና በሀገራችን ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ሲያስመዘግብ የቆየ ግብረ-ሠናይ ተቋም ነው፡፡

በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ጤና ሚኒስቴር የምግብና የሥርዓተ-ምግብ ፖሊሲን እንዲሁም ስትራቴጂን ተቀብሎ ከሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ወደ ተግባር እየቀየረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም እንደ ሀገር መቀንጨርን ለመግታት፣ በድርቅና በግጭት ቀጣና አካባቢ ለሚደረጉ የምግብና የሥርዓተ-ምግብ ድጋፍ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ እና የበርካታ አካላትን ርብርብ እንደሚሻም ነው የጠቆሙት፡፡

በመርሐ-ግብሩ እንደ “ግሎባል አልያንስ” ያሉ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት “ከእርሻ እስከ ገበታ” ያለው የሥርዓተ-ምግብ ዑደት ውስጥ በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ የመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች የተገኙ ሲሆን የድርጅቱን የአመታት ጉዞ የሚያሳይ ፕሮግራምም ለታዳሚዎች መቅረቡን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.