Fana: At a Speed of Life!

የፌደራል መንግስት መቀሌን ጨምሮ ሌሎችንም አካባቢዎች በፍጥነት ተረክቦ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት እንዲያረጋገጥ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የሽግግር ፍትሕ እንዲረጋገጥ፣ የፌደራል መንግስት መቀሌን ጨምሮ ሌሎችንም አካባቢዎች በፍጥነት ተረክቦ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት እንዲያረጋገጥ የትግራይ ክልል ወጣቶችና ምሁራን ጠየቁ፡፡

የትግራይ ክልል ወጣቶችና ምሁራን ለሦስት ቀናት ያካሄዱትን ውይይት ባለስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቀዋል፡፡

በማጠናቀቂያው ላይ ባወጡት የአቋም መግለጫ በፕሪቶሪያ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ደግፈው ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ህወሓት የፌዴራል መንግስት የጀመረውን ጥረት በመደገፍ ለሰላም ስምምነቱ ቁርጠኛ እንዲሆን አሳስበዋል።

ውይይቱ የኢትዮጵያን የለውጥ ሂደት፣ የሰላም ስምምነቱና የትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በማጠቃለያው የተገኙት የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ÷ በክልሉ ለውጥ እንዲመጣ የሚሹ አካላት ላለፉት ሦስት ቀናት ጠንካራ ምክክር ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በዚህም ሀገራዊ ለውጡ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ውጤቶች እየተመዘገቡበት መሆኑ ላይ የጋራ ግንዛቤ እንደተያዘ ተናግረዋል።

በዚህ መነሻም ሀገርን ለማሻገርና በትግራይ ክልል መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የሐሳብ ብዝሃነት እንዲሰፍን፣ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲጎለብት በተደራጀ መንገድ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ መንግስት በትግራይ ክልልና በአጠቃላይ እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የመንግስትን ጥረት የትግራይ ወጣቶችና ምሁራን ስብስብ መደገፍ እንዳለበት ጠቅሰው÷ የትግራይ ክልል ከጦርነት አዙሪት ተላቅቆ በልማትና በሰላም እንዲጓዝ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።

የሰላም ስምምነቱን መንግስት በቁርጠኛነት እየተገበረ መሆኑን በመጥቀስ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የመገንባት ተግባር ላይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መንግስት ለሀገር ሰላምና ልማት ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ ማረጋገጡን ጠቅሰው ይህ የመንግስት ጥረት እንዲሳካም ከጎኑ እንቆማለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የትግራይ ክልልም አሁን ያገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲሆንና ከሀገራዊ ለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብና አጠቃላይ ወጣቱ ከጦርነት አስተሳሰብ በመውጣት ለልማት እንዲነሳሱ የምናደርገውን ጥረት እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።

መንግስት ለሕዝብ እያቀረበ ያለው ሰብዓዊ እርዳታ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የመሰረተ ልማት አገልግሎት ያልተጀመረባቸው አካባቢዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ህወሓት የፌደራል መንግስት የጀመረውን ጥረት በመደገፍ ለሰላም ስምምነቱ ቁርጠኛ እንዲሆን አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.