Fana: At a Speed of Life!

ኮሮና ቫይረስን ለመከላከልም ሆነ የህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት እንደ አንድ ሠራዊት ሆኖ በማሸነፍ ወኔ መነሣት አለበት – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወቅታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
ሙሉ መልዕክታቸውም እንደሚከተለው ቀርቧል።
 
ኮሮናን እንከላከላለን ፤ ግድቡን እንጨርሳለን
 
ውድ የሀገሬ ሕዝቦች
 
የሕዳሴው ግድባችንን ግንባታ የጀመረበትን ዘጠነኛ ዓመት በምናከብርበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ሁለት ጉልህ ፈተናዎች ገጥመውናል፡፡ አንደኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ራሱ የሕዳሴ ግድብ ግንባታችንን የተመለከተ ጉዳይ ነው፡፡
 
ሁላችንም እንደምናውቀው ለእኛ ለሰው ልጆች ትልቁ ጸጋችን ሕይወት ሲሆን ይሄን ድንቅ ጸጋ ሊነጥቀን የኮሮና ወረርሽኝ የእያንዳንዳችን በር እያንኳኳ ከደጃችን ቆሟል።
 
ቫይረሱ የሚተላለፍበት መንገድ ከሰዎች ለሰዎች ንኪኪ ጋር የተገናኘ እና የሚስፋፋበትም መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ ፈጣን እየሆነ እንደመጣ በየዕለቱ የምናየው እውነታ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ወረርሽኙ 201 ሀገራትን አዳርሷል።
 
ከፍተኛ ሥርጭት የተመዘገበባቸው 10 ግንባር ቀደም ሀገራት ከጠቅላላ የኮሮና ተጠቂ 80 በመቶውን ይሸፍናሉ። 90 በመቶ የሚሆነው የኮሮና ሞት የተመዘገበውም በእነዚህ ሀገራት ነው፡፡ የኮሮና የሥርጭት ፍጥነት በኢኮኖሚና በሥልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱትን ሀገራት በከፋ ሁኔታ አዳርሷል።
 
በሀገራችን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ዛሬ 26 ቢሆንም በሚቀጥሉት ሳምንታት ቁጥሩ ሊያሻቅብ ይችል ይሆናል። ምናልባትም ሞት ያጋጥመንም ይሆናል።
 
አሁን በሽታው ከአዲስ አበባ አልፎ በክልል ከተሞችም እየታየ ነው። ለቁጥጥር እንዳያስቸግር አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በሚኖሩባቸው መንደሮች እንዳይገባ ሁላችንም መረባረብ ይኖርብናል፡፡ በመንግሥት በኩል የጥንቃቄ ሕጎችን በጥብቅ ለማስፈጸም፣ የመከላከያና የሕክምና ቁሳቁሶችን በየቦታው ለማዳረስ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።
 
ትምህርት ቤትና መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ ሰዎች የሚበዙባቸውን ስፍራዎችን እንዲዘጉ፣ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲገደቡና ሌሎችም ተያያዥ ርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው። ለእነዚህም ርምጃዎች ተፈጻሚነት አስፈላጊ የሆኑ አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል፡፡
 
ውድ የሀገሬ ሕዝቦች
 
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ከምትጠነቀቅላቸውና በስስት ከምታያቸው ጸጋዎቿ ሁለተኛው የሕዳሴ ግድባችን ነው፡፡ የሕዳሴ ግድባችን ከዕለት ጉርሳችን ቀንሰን በተባበረ ክንድ እየገነባን እዚህ ያደረስነው ብቻ ሳይሆን የማድረግ ዐቅማችንን ያሳየንበት ትልቁ ጸጋችን ነው፡፡
 
ለግድባችን ከፍ ያለ ግምት የምንሰጠው አንድም የሉዓላዊነታችን ምልክት፣ ሁለትም የትሥሥራችን ገመድ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ የፊታችን ክረምት ግንባታው ተገባዶ የውኃ ሙሌት እንጀምራለን ።
 
የኮሮና ወረርሽኝ በዚህ ወቅት መከሠቱ ትኩረታችንን ቀንሶ የሕዳሴ ግድብ ግንባታችን በማጓተት ቀላል የማይባል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ግልጽ ነው፡፡
 
በወረርሽኙ ምክንያት ተዘናግተን የግድብ ባለቤት የመሆን ጉዟችን ማዝገም የለበትም፡፡ እስከዛሬ አሳድገን አሳድገን ፍሬውን ለማየት የጓጓንለት ልጃችንን አሁን በተጋረጠብን አደጋ ምክንያት ፍሬውን ከማየት መገታት የለብንም፡፡
 
በዚህ ወቅት የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት የምናደርገው ትግል በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታት የሚያስችለን ወሳኝ ጎዞ መሆኑ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ መታተም አለበት ።
 
ቤት በመቀመጥና ቶሎ ቶሎ ንጽሕናችንን በመጠበቅ የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል በአንድ በኩል፤ የሕዳሴ ግድባችን፣ ግንባታው ተጠናቆ በቶሎ የውኃ ሙሌቱ እንዲጀመር በዐቅማችን መዋጯችንን መላክ በሌላ በኩል ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡
 
በርግጥ ጊዜያችንን በሥራ ስናሳልፍ የነበርን ሰዎች ለኮሮና ሲባል ቤት ውስጥ መቀመጥ አስቸጋሪ ነው። ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኪሳራዎችን ሊያደርስብንም ይችላል፡፡
 
ሆኖም ግን በሌላ መልኩ ካየነው ይሄንን አጋጣሚ ለመልካም ተግባራት ልናውለው እንችላለን፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅር የሚሰጡበት፤ ባለትዳሮች ስለቀጣይ የሕይወታቸው ምዕራፍ በሰፊው የሚያቅዱበት፤ እንዲሁም ማንበብ የሚፈልጉ ሰዎች ጊዜ ወስደው እንዲያነብቡ፤ የሚጽፉ ሰዎች ጊዜ አግኝተው እንዲያሰላስሉ፣ የሚመራመሩ ሰዎች እንዲመራመሩ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡
 
በዚህ መልኩ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ውጭ ከመውጣት ተቆጥበው ቤታቸው የሚያሳልፉ ዜጎቻችን ራሳቸውንና ሌሎችንም ከክፉው ወረርሽኝ ከማዳን በዘለለ፣ ወረርሽኙ አልፎ ሁሉም ነገር ሲረጋጋ ብዙ መልካም ነገሮችን ማትረፋቸው አይቀርም፡፡
 
ኮሮናን ለመከላከልም ሆነ ግድቡን ለማጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት እንደ አንድ ሠራዊት ሆኖ በማሸነፍ ወኔ መነሣት አለበት።
 
የኮሮና ሥርጭትን ለመግታት ከሰዎች ንክኪ ርቀታችንን በመጠበቅና ራሳችንን መግዛት እንደሚገባን ሁሉ፤ ከሌሎች ሀገራት ርዳታ ለመዳን ለግድባችን ግንባታ ቦንዳችንን መግዛት ይጠበቅብናል፡፡
 
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት እንዲረዳ በሚል በተዘጋጁ የመልእክት መላኪያ ቁጥሮች አማካኝነት ጥቆማና ድጋፍ ስናደርግ በተመሳሳይ ለሕዳሴው ግድብ በ8100 ላይ A ብለን በመላክ የድጋፍ ቤተሰብነታችንን ማረጋገጣችንን እንቀጥላለን፡፡
 
በዚህ መልኩ በመጪው ወራት ውስጥ በዝቅተኛ የጉዳት ሰለባ ኮሮናን ከሀገራችን አጥፍተን፤ በአፋጣኝ ሕዳሴ ግድባችንን የመጀመሪያውን የውኃ ሙሌት አጠናቀን ሁላችንም ስኬታችንን ለማየት እንደምንበቃ አልጠራጠርም፡፡
 
በርግጥም በተባበረ ክንድ ከሠራን ኮሮናንም እንከላከላለን፤ ግድቡንም እንጨርሳለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
መጋቢት 23/ 2012 ዓ.ም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.