Fana: At a Speed of Life!

ኮርፖሬሽኑ ከሦስት ሀገር በቀል ኩባንያዎች ጋር ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ መስራት ከሚፈልጉ ሶስት ሀገር በቀል ኩባንያዎች ጋር በዛሬው ዕለት የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከበርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ አምራች ኩባንያዎችን በማስገባት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለይም የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ፍሰቱ መጨመሩን እና ከ20 በላይ ኩባንያዎች ጋር መፈራረሙም ነው የተመላከተው፡፡

በዛሬው ዕለትም ከጉምሳ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር፣ ከሱጂ ሊያና ዶዮ ማኑፋክቸሪንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር እና ኢምፓክት ፔይንቲንግ ኤንድ ግራፊክስ ጋር የለማ መሬት ውል ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ ከሦስቱ ኩባንያዎች ጋር ተፈራርመዋል።

ስራ አስፈጻሚው በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት ፥ እንደ ሀገር የተያዘውን የሀገር ውስጥ ምርቶችን በራስ ማምረትና ምርቶቻችንን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ እውን ለማድረግ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ አምራች ተቋማት ጋር የልምድ ልውውጥ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግና ኢንዱስትሪዎቻችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ከሀገር በቀል ኩባንያዎችን መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት የውል ስምምነት ሰነድ የፈረሙት ሦስቱ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በጠቅላላው ከ 11 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ኢንሸስትመንት ማስመዝገባቸው ተጠቁሟል፡፡

ከ600 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድልን ይፈጥራሉም ነው የተባለው።

በመራኦል ከድር እና ሲሳይ ዱላ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.