Fana: At a Speed of Life!

በላሊበላ ከተማ በሚከበረው የገና በዓል እስከ 2 ሚሊየን ጎብኚዎች ይጠበቃሉ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘንድሮ በላሊበላ ከተማ በሚከበረው የገና በዓል በአጠቃላይ እስከ ሁለት ሚሊየን የውጭ እና የሀገር ውስጥ እንግዶች እንደሚጠበቁ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳሙ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ታኅሣሥ 29 ቀን 2015 ዓ.ም የሚከበረው የገና በዓል በታሰበው ልክ ስኬታማ እንዲሆን በየዘርፉ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

እየተከናወኑ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን፣ በዓሉን በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የማስተዋወቅ ሥራ፣ ለጎብኚ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን እና ባለድርሻ አካላትን ዝግጁነት ማረጋገጥን ጨምሮ የጎብኚ ፍሰት መረጃ ማደራጀት ተግባራትን ቢሮው በኃላፊነት እየሠራ መሆኑን አብራተዋል፡፡

በዚህም ለጎብኚ የሚመጥኑ ከ45 በላይ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንግዶቻቸውን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የዘንድሮው ገና በዓል በድምቀት መከበር÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በግጭቱ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የጎብኚ ፍሰት እና የቱሪዝም እንቀስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ግጭት የነበረባቸው ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ሰላም መሆናቸውን እና ለጎብኚዎች በማሳወቅ የክልሉን ገጽታ የምንገነባበት ነው ብለዋል፡፡

በዘንድሮው የገና በዓል አከባበር ላይ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች እንዲገኙ በቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ጥሪ መቅረቡንም ጠቁመዋል፡፡

ላሊበላ ከተማ እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ያረጋገጡት አቶ መልካሙ ከዋናው በዓል ቀደም ብሎ÷ የማር ምርት ሲምፖዚየም እንደሚኖርና በላሊበላ ከተማ ውስጥና ዙሪያ እንዲሁም በላስታ ወረዳ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን የሚጎበኙበት ሁኔታ መኖሩን አመላክተዋል፡፡

የቅድመ ዝግጅት ሥራው በቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ በላሊበላ ከተማ አስተዳደር፣ በላስታ ወረዳ አስተዳደር እና በተለያዩ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.