Fana: At a Speed of Life!

በጁገል ዙሪያ የሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች ሊጠናከሩ ይገባል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ቅርስ በሆነው በጁገል ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጁገል ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶችን ዛሬ ተዘዋውረው ተመልክተዋል ።

አቶ ኦርዲን በድሪ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ፥ በጁገል ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች አበረታች ቢሆኑም ስራዎችን ውጤታማ ከማድረግ አንጻር ውስን ክፍተቶች አሉ።

የጁገል ግንብ ሳይበላሽ ተጠብቆ እንዲቆይ ለማስቻል ተቋማትና ባለድርሻ አካላቱ በጋራ በመቀናጀት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

አንዳንድ ተቋማት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ እንደሚገኙ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ ሌሎች ተቋማትም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ውጤታማ ተግባራትን ሊያከናውኑ ይገባል ነው ያሉት።

ሁሉም ተቋማት የባለቤትነት ስሜትን በመላበስና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት አካባቢውን በተሻለ አቅም ማልማት እንደሚያስፈልግም ነው የተነሳው።

የጁገል ዙሪያን ከማልማት ጋር በተያያዘ ተቋማቱ ያላቸውን አቅምና የሰው ኃይል በመጠቀም የተጀመሩ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በቀጣይ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ በፍጥነት ሊያጠናቅቁ እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጠዋል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.