Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት ይሰራል – አቶ ኡሞድ ኡጅሉ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጅሉ ገለጹ፡፡
በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የተመራ ቡድን በጋምቤላ ወረዳ ፑኮንግ ቀበሌ ያለውን የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር ምልከታ አካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት ይሰራል።
በተለይም በጋምቤላ ወረዳ ከአቦል ከተማ ወደ ፑኮንግ የሚወስደው መንገድ በመበላሸቱና አንድ ድልድይ ጠቦ በመሰራቱ ምክንያት በቀበሌው ነዋሪ ላይ ከፍተኛ መጉላላት እየደረሰ እንደሚገኝ እንደተረዱም ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም መንገዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠግኖ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ጠቁመው ፥ ድልድዩም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መፍትሔ እንደሚያገኝ ገልፀዋል።
በክልሉ ሰፊ የመሠረተ ልማት ጥያቄ መኖሩን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የክልሉ ህዝብ የመንግስትን የሰላም ጥረት እንዲያግዝም ጠይቀዋል።
በበጀት ዓመቱ የዘገዩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃትና ሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከፍተኛ አመራሮቹ በመጠገን ላይ ያለውን በጋምቤላ ወረዳ ከአቦል ከተማ አቦል ኪር ቀበሌ የሚወስደውን መንገድ ጎብኝተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.