Fana: At a Speed of Life!

ዕጽ በማዘዋወር የተከሰሱ ብራዚላዊ እንስቶች በፅኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያየ ጊዜ የኮኬይን ዕፅ ደብቀው ለማሳለፍ ሲሉ በተደረገ ፍተሻ የተያዙት ብራዚላዊ እንስቶች እያንዳንዳቸው በ10 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር መቀጣታቸው ተገለጸ፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ኤልዳ ሪጂና ሳንቶስ የተባለችው ብራዚላዊት ተከሳሽ መነሻዋን ብራዚል ሳኦፖሎ አድርጋ ወደ ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ለመጓዝ መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለትራንዚት ስታርፍ በተደረገ ፍተሻ 1ሺህ 76 ጥቅል ፍሬ የሚመዝን 23 ሺህ 73 ግራም ኮኬይን እፅ ደብቃ ለማሳለፍ ስትል ተይዛለች፡፡

በፈፀመችው እፆችን ማዘዋወር ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተባት ሲሆን ፥ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት ቀርባ ክሱ ተነቦላት የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ እንዳለችም ነው የተገለጸው፡፡

ዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ማቅረብ ሳያስፈልገው ባመነችው መሰረት የጥፋተኝነት ፍርድ እንዲሰጥ ጠይቆ ፍርድ ቤቱም ተከሳሿ በተከሰሰችበት ድንጋጌ ስር በዝርዝር ያመነች በመሆኑ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡

በዚህም ፍርድ ቤቱ ተከሳሽን በ10 ዓመት ፅኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር እንድትቀጣ መወሰኑን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ 14 ሺህ 412 ግራም የሚመዝን የኮኬይን እፅ በተደረገ ፍተሻ በሻንጣዋ ውስጥ የተገኘባት ናዲራ ጋብርኤላ የተባለችው ብራዚላዊት በፈፀመችው አደገኛ እጽ የማዘዋወር ወንጀል ድርጊት በ10 ዓመት ፅኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር እንድትቀጣ ተወስኗል፡፡

ተከሳሿ ኮኬይን እፅ በሻንጣዋ ውስጥ ደብቃ መነሻዋን ብራዚል ሳኦፖሎ ከተማ አድርጋ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር መንገድ ነሀሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም ለትራንዚት ስታርፍ 533 ፍሬ ጥቅል ኮኬይን መያዟ በፍተሻ ታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.