Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 30 ዓመታት የእናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት ሞት ምጣኔ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 30 ዓመታት የእናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት ሞት ምጣኔ ቅናሽ ማሳየቱን ጥናት አመላከተ፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር እና ካውንት ዳውን 2030 የጥናት ምርምር ቡድን ጋር በመተባበር ባለፉት 30 ዓመታት የተመዘገበውን የእናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት የጤና ክብካቤ ሽፋን፣ የሞት መጠን ቅነሳ ሪፖርት ይፋ አድርገዋል፡፡

በሪፖርቱ የእናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት ሞት ቅነሳ በፈረንጆቹ ከ1990 እስከ 2019 እንዲሁም ከ2016 እስከ 2020 የጤና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም ግምገማዊ ጥናት የተካሄዱ የጥናትና ምርምር ግኝቶች ይፋ ሆነዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ÷በካውንት ዳውን 2030 የተሠሩ ጥናቶች ባለፉት30 ዓመታት በሀገሪቱ የእናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት ሞትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ የስነ ተዋልዶ ጨቅላ ሕፃናት እና ልጆች ጤና ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበሯ ከ2000 እስከ 2019 የእናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

በፈረንጆቹ 2000 በ100 ሺህ በሕይወት ከወለዱ እናቶች ከነበረው1ሺህ 30 የሞት ምጣኔ በ2017 ወደ 401 የደረሰ ሲሆን÷ ይህም በ61 በመቶ መቀነስ መቻሉን በተለይም በቅርብ 10 ዓመታት ውስጥ ከ2005 እስከ 2017 በግማሽ መቀነሱን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡

በተያያዘም በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕጻናት ሞት በ2000 ከነበረው 140 ሺህ የሞት መጠን በ2019 ወደ 100 ሺህ መቀነሱ ተጠቁሟል፡፡

ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ላሉ ሕጻናት በ1990 ላይ የሞት መጠን 31 በመቶ ከነበረበት በ2010፣ 47 በመቶ እንዲሁም በ2019 ከግማሽ በላይ (56 በመቶ) መድረሱ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ጥናቱ የእናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት ሞት ቅነሳ ላይ ሲካሄዱ የነበሩት የተለያዩ ሥራዎች የተሻለ ውጤት እንዳስመዘገቡ ማመላከቱን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.