Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ በጸሐይ ሃይል የሚሰሩ 9 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ለመስኖ ልማት ምቹ በሆኑ አካባቢዎች በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ ዘጠኝ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ይፋ ማድረጉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቀ።
 
ሚኒስቴሩ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የፕሮጀክቱን አጀማመር አስመልክቶ ዛሬ ከነዋሪዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
 
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ በውይይቱ ላይ እንዳሉት÷ ፕሮጀክቶቹ በመስኖ የሚያለሙ አርሶ አደሮችን የገንዘብ ወጪና ጉልበት የሚቀንሱ ናቸው ።
 
የፀሐይ ሃይልን የሚጠቀሙት ዘጠኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ እና በሲዳማ ክልሎች እንደሚተገበሩም ገልፀዋል።
 
ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ለመስኖ የሚውል የገፅና የከርሰ ምድር ውሃ ያለባቸው ቀበሌዎች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
 
በፕሮጀክቱ የሚገኘው የፀሐይ ሀይል ለመስኖ አገልግሎት የሚውለውን ውሃ ከጉድጓድ ስቦ ለማሰራጨት ከሚኖረው ጥቅም ባሻገር ሰፈሮችን የሀይል ተጠቅሚ ያደርጋል ብለዋል።
 
ይህም ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ፣ ለወፍጮ አገልግሎትና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለማስፋፋት ስለሚውል ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ፕሮጀክቶቹ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ ከ15 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.