Fana: At a Speed of Life!

ለቁልቢ ገብርኤል ክብረ በዓል በቂ ዝግጅት መደረጉን የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል ክብረ በዓል በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት ማድረጉን የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡

በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ፣ ከሐረሪ ክልል ፖሊስ እንዲሁም ከድሬዳዋ ፖሊስ የተውጣጥቶ በዕዝ የሚመራ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከአካባቢው አስተዳደር፣ ከሀይማኖት አባቶች እና ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ዝግጅት ተደርጓል ነው ያለው፡፡

ታኅሣሥ 19 ቀን 2015 ዓ.ም የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል ክብረ በዓል በሰላም እንዲከበር በተለይ የኦነግ ሸኔ ሴሎች የሚንቀሳቀሱባቸውን ተጋላጭና ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ አካባቢዎችን በመለየትና በቂ ዝግጅት በማድረግ ግብረረ ኃይሉ ስምሪት ወስዶ ወደ ተግባር መገባቱን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የአካባቢው ኅብረተሰብ ለበዓሉ ታዳሚዎች ቅድሚያ በመስጠት የተለመደውን ቀና ትብብር እንዲያደርግ እና ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አስጊ ሁኔታዎችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች በፍጥነት ጥቆማ በመስጠት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.