Fana: At a Speed of Life!

ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የፈጸመችው ፍቺ 33 ቢሊየን ዮሮ እንዳሳጣት ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት ለቃ መውጣቷ (ብሪኤግዚት) 33 ቢሊየን ዮሮ እንዳሳጣት አንድ ጥናት አመላከተ።

መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ቡድን ያጠናው ጥናት ብሪታንያ ህብረቱን ለቃ መውጣቷ በኢኮኖሚያዊ እድገቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን አመላክቷል።

እንደ ጥናቱ ከሆነ ብሪታንያ በህብረቱ ውስጥ ብትቆይ ኢኮኖሚያዊ እድገቷ ካለበት በ5 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ያለ ሊሆን ይችል ነበር።

ይሁን እንጅ ብሪታንያ ህብረቱን ለቃ ከወጣች በኋላ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት እድገቷ በህብረቱ ውስጥ ብትቆይ ይሆን ከነበረው የ5 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ አሳይቷልም ነው ያለው።

ይህም በገንዘብ ሲተመን 33 ቢሊየን ዩሮ ወይም 40 ቢሊየን ዶላር መሆኑን የአውሮፓ ሪፎርም ማዕከል ያደረገውን ጥናት ውጤት ዋቢ አድርጎ አር ቲ ዘግቧል።

ማዕከሉ አሁን ላይ በሌሎች የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ያለውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ዳታዎችን መሰረት አድርጎ ባወጣው መረጃ፥ ብሪታንያ ህብረቱን ባትለቅ ኖሮ ምናልባትም የአህጉሪቱ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ልትሆን እንደምትችልም አስረድቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ህብረቱን መልቀቋ በኢንቨስትመንት እና ንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሏልም ነው ያለው።

በዚህ ሳቢያ የኢንቨስትመንት እድገቱ በከፍተኛ ሁኔታ ቅናሽ ሲያሳይ የሸቀጦች ንግድም በሰባት በመቶ ወርዷል ነው የተባለው።

የሀገሪቱ ህብረቱን መልቀቅ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖም ለከፍተኛ የግብር ጭማሪ እንደዳረጋቸውም ነው ማዕከሉ የገለጸው።

ለመሰረታዊ አገልግሎቶች ማስፈጸሚያ በቂ ገንዘብ ለማግኘት፥ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ዝቅተኛ ገቢ በግብር ጭማሪ ማካካስ እንደ አማራጭ መወሰዱንም ነው የሚገልጸው።

ለዚህ ደግሞ ሪሺ ሱናክ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ያደረጉትን የግብር ጭማሪ በማሳያነት አንስቷል።

አሁን ላይ ብሪታንያ ህብረቱን ለቃ መውጣቷ በኢኮኖሚዋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ለማለት ችኮላ ቢመስልም ተንታኞች ግን የዚህ ውጤት ተፅዕኖ በቀጣዮቹ አስርት አመታት ጎልቶ ይታያል ባይ ናቸው።

የሀገሪቱን የበጀት ጉዳዮች የሚከታተለው ጽህፈት ቤት “ብሪኤግዚት” እስከ ፈረንጆቹ 2031 ባለው ጊዜ ውስጥ የብሪታንያን ኢኮኖሚያዊ እድገት በ4 በመቶ (በ100 ቢሊየን ዩሮ) ይቀንሰዋል የሚል ትንበያ አስቀምጧል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ ብሪታንያ ከህብረቱ ጋር የፈጸመችው ፍቺ ጉዳት ከዚህም የከፋ ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.