Fana: At a Speed of Life!

ከሰኞ ጀምሮ 6 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ወደ አክሱም ዩኒቨርሲቲ ያቀናል

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ሥድስት አባላትን ያካተተ የባለሙያዎች ቡድን ወደ አክሱም ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ምልከታ ሊያደርግ ነው፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደር እና መሰረተ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በግጭቱ ምክንያት ሥራ ያቋረጡ የአክሱም፣ ራያ፣ አዲግራት እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ አገልግሎት ለመመለሥ እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤት ኮሚቴ ተቋቁሞ ዝርዝር ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ነዉ፡፡

ዩኒቨርሲቲዎቹ ዳግም የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጀምሩ የሚያስችላቸውን መሰረታዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው የሚለውን የመለየት ሥራ መከናወኑንም አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታም ከአክሱም እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ዳግም ወደ አገልግሎት በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ ንግግር መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የስልክና ሌሎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ሲሟሉ ከመቀሌ እና አዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት እንደሚጀምሩ አመላክተዋል፡፡

አሁን በአክሱም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ፥ ሥድስት አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ከሰኞ ጀምሮ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ዋናውን ግቢ ጨምሮ ዐድዋ እና ሽረ ግቢዎችን በሥፍራው ተገኝቶ ምልከታ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በተዘጋጀው መመዘኛ (ቸክሊስት) መሰረትም ግቢዎቹ በሰው ኃይል፣ በመሰረተ ልማት፣ በቤተ ሙከራ፣ በመኝታና መማሪያ ክፍሎች፣ በማስተማሪያ ሆስፒታል፣ በቤተ መጻሕፍት እና በሰርቶ ማሳያ ለተማሪ እና መምህራን አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው መማር ማስተማር ሥራውን ለማስጀመር የሚያስችለውን ሁኔታ በጥልቀት ይመለከታል፡፡

የባለሙያዎች ቡድን በሚያመጣው መረጃና ምክረ ሐሳብ መሰረት ዩኒቨርሲቲውን ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ትምህርት ሚኒስቴር እንደሚያመቻች እና ለመማር ማስተማር ዝግጁ መሆናቸው ሲረጋገጥ ለተማሪዎች ክፍት እንደሚሆንም አረጋግጠዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.