Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የክልሉ መሬት ቢሮ የገጠርንም ሆነ የከተማን መሬት በአግባቡ በመመዝገብና አጠቃቀምን በመወሰን በእቅድ እንዲተዳደር እያደረገ ነው ተብሏል፡፡

የዜጎችን የመጠቀም መብትና ዋስትናን ለማረጋገጥም ወቅታዊ መረጃን የመያዝ ሂደትን እያጠናከረ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ በመድረኩ እንደገለፁት÷ መሬት የሁሉም ልማት መሰረት ነው።

መሬት የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካም አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም በዜጎች በኩል ጥያቄዎች ሲቀርቡ በመንግስት በኩል የመፍትሄ ምላሾችን ለመስጠት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።

በመሬት ዙሪያ የሚያጋጥሙ ክርክሮችን በትክክለኛና በተደራጀ መረጃ ውሳኔ መስጠት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።

የቢሮ ሀላፊው አቶ ሲሳይ ዳምጤ በበኩላቸው÷ በቀጣይ ሁለትና ሶስት አመታት የገጠርና የከተማ መሬት አስተዳደርን ዘመናዊ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በክልሉ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፥ ዘመናዊ የካዳስተር ስራና ምዝገባ እንዲከናወንላቸው ከተለዩ 148 ወረዳዎች ለ112ቱ መሰራቱን ተናግረዋል።

ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ከካሳና ከግምት ተግባራት መሰብሰብ እንደተቻለ በመጥቀስም፥ የአስተዳደር ስራው ከወረቀት ወጥቶ ወደ ዲጂታል በመቀየሩ ፈጣን አስተዳደራዊ አገልግሎት ለመስጠት መቻሉን አንስተዋል።

የውይይቱ ዋነኛ አላማ በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ ለማበጀት ነው ተብሏል።

በሙሉጌታ ደሴ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.