Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ያስገነባው የፀሐይ ኃይል ምርቶች መፈተሻ ላቦራቶሪ ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የ250 ሺህ ዶላር ድጋፍ ያስገነባው የፀሐይ ኃይል ምርቶች መፈተሻ ላቦራቶሪ ሥራ ጀመረ።

ላቦራቶሪው እስከ 350 ዋት የሚደርሱ የፀሐይ ኃይል ምርቶችን ለመፈተሽ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ እንደገለጹት÷ ከውጭ የሚገቡና በሀገር ውስጥ የሚመረቱት የፀሐይ ኃይል አቅርቦትን ጥራት ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።

ይህንን ተከትሎም አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የ250 ሺህ ዶላር ድጋፍ ዘመናዊ የፀሐይ ኃይል ምርቶች መፈተሻ ላቦራቶሪ ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል።

ላቦራቶሪው ለገጠር ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚውሉ የፀሐይ ኃይል ምርቶችን የመፈተሽ፣ የመመርመርና የምስክር ወረቀት መስጠት እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡

ምርቶች ኢትዮጵያ ያወጣቻቸውን አስገዳጅ መስፈርቶች ማሟላታቸውን የቅድመ ጭነት ፍተሻ በማድረግ በሚሰጡት ማረጋገጫ ምርቶቹ እንደሚገቡም ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ አሁን ላይ በዘመናዊ የፍተሻ ቴክኖሎጂዎች የተደራጁ ዘጠኝ የፍተሻ ላቦራቶሪዎች እንዳሉትም ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.