Fana: At a Speed of Life!

የገዳ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገዳ ባንክ የሀገሪቱን የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች በማሟላት ዛሬ በይፋ ሥራውን ጀምሯል፡፡

የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የተካሔደው ጎተራ አካባቢ ባንኩ ባስገነባው ሕንጻ ነው፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያሉ ነባር እና አዲስ ባንኮች ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

ባንኮቹ በተለይም የግሉን ዘርፍ በብድር በመደገፍ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቁመው ኢኮኖሚው በብዛት በብድር የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ ባንኮቹ የሚሰጡት የብድር መጠን እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የብድሩ ምንጭም ከቁጠባ እንደመሆኑ ባንኮቹ ቁጠባን መሰረታዊ ሥራ አድርገው ሊወስዱት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ገዳ ባንክም ተደራሽነቱን በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍል በማድረግ በተለይም ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል።

ብሔራዊ ባንክ ለባንኩ ዓላማና ራዕይ ስኬት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው÷ ባንኩ በኢኮኖሚው ውስጥ ገብቶ የራሱን አስተዋጽኦ የማበርከት ከፍተኛ እድል እንዳለው ጠቁመዋል።

ኢኮኖሚያችንን እያሳደግን ከዓለም ጋር ልንወዳደር ይገባል ያሉት አቶ ሽመልስ÷ ይህንን ለማሳካት በእውቀት ላይ ተመስርቶ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ክልላዊ መንግሥቱ ባንኩ ለስኬት እንዲበቃ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወልዴ ቡልቱ፤ ባንኩ በቀጣይ በሰላሳ ቅርንጫፎች አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ባንኩ ወደ ገበያው በሚገባበት ወቅትም እድገትን የሚያሳልጡ አሰራሮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.