Fana: At a Speed of Life!

በድንበር አካባቢ ያለውን ሰላም ለማስቀጠል ቀጣናውን በንግድ፣ በመንገድና በቱሪዝም ማስተሳሰር እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአጎራባች ሀገራት ድንበር አካባቢ ያለውን ሰላም ለማስቀጠል ቀጣናውን በንግድ፣ በመንገድና በቱሪዝም ማስተሳሰር እንደሚገባ የኢፌዲሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ፡፡

“ኤኩሞሞር ለቀጣናዊ ትስስር” በሚል መሪ ሐሳብ የዑጋንዳ፣ ኬኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች የተሳተፉበት የባህል፣ የቱሪዝም እና የሰላም ፌስቲቫል በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ ካንጋቴን ከተማ ተካሂዷል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተሳተፉት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ÷ በአጎራባች ሀገራት ድንበር አካባቢ ያለውን ሰላም ለማስቀጠል ቀጣናውን በንግድ፣ በመንገድ መሰረተ ልማት፣ በቱሪዝም እና በሌሎች ዘላቂ የልማት ሥራዎች በማስተሳሰር ሕዝቦችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተሳተፉበት የ “ኤኩሞሞር ፌስቲቫል” ኢትዮጵያ በውጭ ዲፕሎማሲዋ ለጀመረችው ቀጣናዊ ትስስር ስኬታማነት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኤኩሞሞር ፌስቲቫል ዘላቂ ሰላምና ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር በኩል ሚናው የላቀ መሆኑንም ነው አቶ ኃይለማርያም የተናገሩት፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በድንበር አካባቢ የታየው ሰላምና የሕዝብ ለሕዝብ ቅርርብ የኤኩሞሞር ፌስቲቫል ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።

የደቡብ ክልል ዋና አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ፋጤ ሰርመሎ በበኩላቸው÷ የኤኩሞሞር ፌስቲቫል ኢትዮጵያ በውጭ ዲፕሎማሲ ለጀመረችው ቀጣናዊ ትስስር ስኬታማነት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

በተከበረው የሰላም ፌስቲቫል ላይ የክልልና የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች፣ ከምዕራብ ኢትዮጵያና ከደቡብ ክልሎች የመጡ የክብር እንግዶችን ጨምሮ÷ ከዑጋንዳ-ካራሞጃንግ፣ ከኬኒያ-ቱርካና፣ ከደቡብ ሱዳን-ቶፖሳና ጂዬ በመባል የሚጠሩና ከኛንጋቶም ማህበረሰብ ጋር ተመሳሳይ ቋንቋ ተጋሪ የሆኑና ተቀራራቢ ባህል ያላቸው ማህበረሰቦች እንዲሁም የቀጣናው አስተዳዳሪዎች ታድመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.