Fana: At a Speed of Life!

በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብ መገንባት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቀዳሚ ተልዕኮ ነው – አቶ አድማሱ ዳምጠው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብ መገንባት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቀዳሚ ተልዕኮ ነው ሲሉ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው ተናገሩ፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቅዳሜ ልዩ 120 ደቂቃ የሬዲዮ ዜና ፕሮግራም በዛሬው እለት በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡

ይህን አስመልክተው መልዕክት ያስተላለፉት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው፥ ፋና የህዝቦችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቀስቃሴዎች መሰረት ባደረገ መልኩ ላለፉት 28 አመታት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ጣቢያው ከ28 አመታት በፊት በሬዲዮ ስርጭት አግልግሎት መሰጠት መጀመሩን ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ አሁን ላይ በቴሌቪዥን እና በዲጅታል ሚዲያ አማራጮች ወደ ህዝብ እየደረሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በየጊዜው በሚከሰቱ የተለያዩ ለውጦች ፣ በትውልዱ መካከል መቀራረብ እንዲኖር እና ሀገር አሁን የደረሰችበት የእድገት ደረጃ እንድትደርስ ፋና የራሱን ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡

ማዝናናት እና ማስተማር፣ መልካም ተሞክሮዎች በየአካባቢው እንዲስፋፉ ማድረግ ፣ የህብረተሰብ የእድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ወደ ሚመለከተው አካል እንዲደርሱ እና መፍትሄ እንዲያገኙ ማደረግ እንዲሁም በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብ መገንባት የፋና ተልዕኮዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ዛሬ በጀመረው የቅዳሜ ልዩ 120 ደቂቃ የሬዲዮ ዜና ፕሮግራም በልዩ አቀራርብ የተለያዩ የማህበራዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ፕሮግራሙ በመጀመሩ ለጣቢያው አድማጮች እና ጋዜጠኞች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥  ጋዜጠኞች የህዝብን የመረጃ ጥማት በማርካት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲረጋገጥ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.