Fana: At a Speed of Life!

ለሌማት ትሩፋት ስኬታማነት ድጋፍ እንደሚደርግ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩቱ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት ለጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐግብር ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር፣ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ የአማራ ክልል ግብርና ምርምር እና ዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ያዘጋጁት የሌማት ትሩፋት ያተኮረ ዐውደ ጥናት ዛሬ በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል።

የኢንስቲትዩቱ መሪ ተመራማሪ ዶክተር ታደለ ደሴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷የኢትዮጵያ መንግስት ለሌማት ትሩፋት ያሳየው ቁርጠኝነት ሀገሪቱ ያላትን የእንስሳት ሃብት ምርታማነት ለማሳደግ የጎላ ድርሻ አለው።

ኢትዮጵያ በርካታ የእንስሳት ሃብት ቢኖራትም ከዚህ ቀደም ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ ከቁጥር ባለፈ በጥራትም ሆነ በመጠን ምርታማ በመሆን ረገድ ሰፊ ክፍተት ነበር ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህም የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል ባለመቻሉ፣ በቂ የሆነ የመኖ አቅርቦትና የእንስሳት ጤና እንክብካቤ ችግሮች በመኖራቸው ነው ብለዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩ ለእንስሳት ሃብት ምርታማነት ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም ቀደም ሲል በስፋት ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች እንዲቃለሉ ያግዛል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስና አዳዲስ አሠራሮችን ተደራሽ በማድረግ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.