Fana: At a Speed of Life!

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በቻን ውድድር የቪዲዮ ረዳት ዳኛ ሆነው እንዲያጫውቱ ተመረጡ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ሰባተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) በቪዲዮ ረዳትነት እንዲያጫውቱ ተመርጠዋል።
 
በሀገር ውስጥ ሊግ የሚሳተፉ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ከጥር 5 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ይከናወናል።
 
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በቻን ውድድር በቪዲዮ ረዳት ዳኝነት(ቫር) እንዲያጫውቱ መምረጡን ይፋ አድርጓል።
 
ባምላክ በቫር ዳኝነት መመረጡን የሚያሳይ መልዕክት ከካፍ የደረሰው መሆኑን አረጋግጧል፡፡
 
የ40 ዓመቱ ኢንተርናሽናል ዳኛ በፊፋ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ ያገኘው በፈረንጆቹ በ2009 ሲሆን÷ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ውድድሮች በመዳኘት የረጅም ጊዜ ልምድ አካብቷል።
 
ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በ2020 በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የእግር ኳስ ውድድርን በዋና ዳኝነት መርተዋል።
 
ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ካፍ በአልጄሪያው ውድድር በቫር ዳኝነት ከተመረጡ 12 ዳኞች አንዱ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.