Fana: At a Speed of Life!

ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በ15 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወንጀል በተመሰረተበት ሶስት ተደራራቢ ክሶች በ15 ዓመት ጽኑ እስራትና በ105 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተቀጣ፡፡
 
በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ፥ መሀመድ አህመድ የተባለው ኤርትራዊ ዜግነትያለው እና የመኖሪያ አድራሻው አዲስ አበባ ከተማ የነበረው ግለሰብ በፈጸመው ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ የወንጀል ችሎት ሶስት ተደራራቢ ክሶች መስርቶ ክርክሩን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
 
ተከሳሽ በሶስቱም ክሶች በሰው መነገድ እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ/ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 8/1 እና 3/መ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ነው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው፡፡
 
ተከሳሽ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረዓበሮቹ ጋር በመሆን ሳላህ ዑመር አህመድ የተባለውን እና በወንጀል ድርጊቱ ለሞት የተዳረገውን ግለሰብ በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም በህገ-ወጥ ጉዞው ላይ የነበሩ ሌሎች 2 ግለሰቦችን ከኢትዮጵያ ግዛት ወደ ሱዳን ድንበር ለማሻገር እያንዳንዳቸው 700 የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍሉት እና ወደ ሱዳን የሚወስዳቸውን መኪና እንደሚልክላቸው ተስማምቷል፡፡
 
ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከረፋድ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ለጊዜው ያልተያዘው ዑመር የተባለው ግብረ አበሩ ተከሳሽ ልኮኝ ነው ተዘጋጁ መኪና ይመጣል በማለት እንዲዘጋጁ በማድረግ 3፡30 ሰዓት ሲሆን ሟች እና ሌሎች 2 ግለሰቦች ወደ ነበሩበት ወደ ጎንደር ከተማ በተከሳሽ በኩል መኪና ተልኮላቸው ወደ ሱዳን መጓዝ ጀመሩ፡፡
 
በጉዞ ላይ እያሉ አብርሀ ጅራ ወደተባለ ቦታ ሲቃረቡ የመኪናው ሾፌር እና ረዳት አብርሀ ጅራ ኬላ በመሆኑ ፍተሻ ስላለ በሞተር ነው የምትሄዱት በማለት ከመኪና ካስወረዷቸው በኋላ ለጊዜው ላልተያዙ እና በቁጥር 5 ለሆኑ ግብረ አበሮቻቸው አስረክቧቸዋል፡፡
 
የተረከቡት ግለሰቦችም ጉዞውን በሞተር እንዲሁም በእግር ይዘዋቸው ከሄዱ በኋላ ስፍራው መለየት ባልተቻለ ቦታ ሲደርሱ ተጓዦቹ ለተከሳሽ ደውለው ስለሁኔታው ሲናገሩ በሌሎች ሰዎች እጅ እንደወደቁና የእሱ ሰዎች ባለመሆናቸው እንዲያመልጡ ሲነግራቸው ሶስቱም ለማምለጥ ሲሞክሩ ግለሰቦቹ በያዙት መሳሪያ ሲተኩሱ ሳላህ ዑመር አህመድ የተባለውን ሟች የቀኝ እግር ጉልበቱ ላይ በመምታት ብዙ ደም ስለፈሰሰው ህይወቱ አልፏል፡፡
 
በመሆኑም ተከሳሽ በፈፀመው ሰዎችን ድንበር የማሻገር ወንጀል በዋና ወንጀል አድራጊነት ሶስት ተደራራቢ ክሶች እንደተመሰረቱበት የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ላይ ተመላክቷል፡፡
 
ተከሳሽ ክሱ በፍርድ ቤት ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ የተከራከረ ሲሆን ከሳሽ ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የወንጀሉን መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ማስረጃ ለችሎቱ እንዲሰማ አድርጓል፡፡
 
ችሎቱም ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን ማሰማቱን ተከትሎ ተከሳሽን የዐቃቤ ህግን ማስረጃ እንዲያስተባብል ብይን የሰጠ መሆኑን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ተከሳሽ ወንጀሉን አለመፈጸሜን ያስረዱልኛል ያላቸውን የመከላከያ ምስክሮች አቅርቦ ቢያሰማም የቀረበበትን ክስ እና ማስረጃ ያላስተባበለ በመሆኑ በቀረበበት 3 ክሶች የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበት በ15 ዓመት ጽኑ እስራትና በ105 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.