Fana: At a Speed of Life!

አሰሪዋን የገደለችው ግለሰብ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ “የወር ደመወዝ አልተከፈለኝም” በሚል ቂም ተነሳስታ አሰሪዋን ገድላች የተባለችው አበቡ ሙላቴ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ውሳኔ ተላለፈ፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ እየሠራች እያለ “የተወሰነ ወራት የወር ደመወዝ ክፍያ አልተከፈለኝም” በሚል ምክንያት ቂም ይዛ አሠሪዋን በመደብደብ ህይወቷ እንዲያልፍ አድርጋለች ባላት ግለሰብ ላይ ክስ መስርቶባት በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ማድረጉን አስታውቋል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው÷ ተከሳሽ አበቡ ሙላቴ ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 10፡45 ሰዓት ገደማ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አስኮ አዲስ ሰፈር ሊዝ መንደር አካባቢ አሰሪዋ የነበሩትን ወይዘሮ ፋሲካ ተሾመን በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲልፍ አድርጋለች፡፡

ተከሳሽ ክሱ ተነቦላት የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ ያለች ሲሆን÷ ዐቃቤ ሕግም ተከሳሿ የተከሰሰችበትን የወንጀል ድርጊት እንደ ክሱ ሙሉ በሙሉ ማመኗን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በተከሳሿ ላይ በደረጃ 2 እርከን 39 ስር መነሻ ቅጣት በመያዝ፣ ተከሳሽ ወንጀሉን ያመነች በመሆኑ፣ 1 የቅጣት ማቅለያ ተይዞላት በእርከን 38 ስር በማሳረፍ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ እንዲሁም ማህበራዊ መብቶቿ ለዘወትር እንዲሻሩ ሲል ወስኖባታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.