Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካን በመታት የበረዶ ማዕበል የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 49 ማሻቀቡ ተሰማ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ በተከሰተው ከፍተኛ ቅዝቃዜና የበረዶ ማዕበል ሳቢያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 49 ማሻቀቡ ተሰምቷል፡፡

በፈረንጆች የገና በዓል ዋዜማ ጀምሮ በተከሰተ የበረዶ ማዕበል 49 ሰዎች መሞታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

የሞቃታማ አየር፣ እርጥበት አዘል እና እጅግ ቀዝቃዛ ደረቅ አየር የሚፈጥሩት ውህደት ለበረዶ ማዕበሉ ምክንያት መሆኑን የአሜሪካ ብሄራዊ የሚቲዮሮሎጅ አገልግሎት አስታውቋል።

ከዚህ ባለፈም ከፓሲፊክ ውቅያኖስ በሚነሳ እጅግ እርጥበት አዘል አየርና ከወንዞች አካባቢ የሚነፍሰው ሞቃታማ እና ደረቅ አየር ሳቢያ ከባድ ዝናብ እና በረዶ እንዲጥል ምክንያት መሆኑንም ነው የአገልግሎቱ መረጃ የሚያመላክተው።

የበረዶ ማዕበሉና ውሽንፍሩ ከአሜሪካ በተጨማሪ በካናዳ ከባድ ጉዳት ማስከተሉም ነው የተነገረው።

ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ቡፋሎ ምዕራብ ኒው ዮርክ ብቻ 27 ሰዎች መሞታቸው ነው የተዘገበው፡፡

በቡፋሎ ባሳለፍነው እሁድ 4 ጫማ ከፍታ ወይም 1 ነጥብ 25 ሜትር ከፍታ ያለው የበረዶ ግግር ተከስቶ ነበር።

አብዛኛዎቹ የአደጋው ሰለባዎች በዚሁ ቀን በመኪናቸው ውስጥ እና በቤታቸው ውስጥ እንዲሁም ግግር በረዶውን በማስወገድ ላይ እያሉ ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ነው የተዘገበው፡፡

ማዕበሉ የአሜሪካን ምስራቅ የባህር ዳርቻ በካናዳ አቅራቢያ ከሚገኙት ታላላቅ ሀይቆች እስከ ሪዮ ግራንዴ በአሜሪካ እና እና ሜክሲኮ ድንበር እንደደረሰ የሀገሪቱ የአየር ንብረት መረጃ ማመላከቱን አር ቲ ዘግቧል፡፡

በበረዶ ማዕበሉ ሳቢያ ከ1 ንጥብ 7 ሚሊየን በላይ አሜሪካውያን ለኃይል አቅርቦት እጥረት ሲዳረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ የአውሮፕላን በረራዎችም ተሰርዘዋል ነው የተባለው።

በአንድ ቀን ብቻ 3 ሺህ በረራዎች ሲሰረዙ 4 ሺህ በረራዎች ደግሞ ተላልፈዋል።

የአየር ትንበያ ባለሙያዎች “በትውልድ አንድ ጊዜ የሚያጋጥም” ያሉት ክስተት የአሜሪካ የጋዝ ምርት በ10 በመቶ እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑም ነው የተነገረው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.