Fana: At a Speed of Life!

ሕፃናት ላይ የሚከሰት የኩላሊት ህመም ምልክቶች እና መከላከያዎች

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕፃናት በተፈጥሮ አልያም በክትትል ማነስ ለኩላሊት ህመም ሊጋለጡ እንደሚችሉ የሕፃናት ስፔሻሊሰት ዶክተር ቤዛዬ አበበ ይናገራሉ፡፡

ሽንት ማሸናት፣ ሰገራ አድርገው በአግባቡ የመጠረግ እና የመሳሰሉ ሊማሩ የሚገቧቸው ሁኔታዎች ባለመስተካከል ምክንያት ለኢንፌክሽን በመጋለጥ ለኩላሊት ህመም ችግር ሊዳርግ እንደሚችል ያብራራሉ፡፡

ውሀ መጠማት፣ እንደተቅማጥ እና ትውከት ያሉ ችግሮችም የኩላሊት መድከም ሊያመጡ እንደሚችሉም ነው የሚያነሱት፡፡

እንደ ሳንባ ምች ላሉ እና ለሌላ በሽታዎች የሚሰጣቸው መድሃኒቶችም በተጓዳኝ ኩላሊት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ ሲሉም ነው ዶክተር ቤዛዬ የሚገልፁት፡፡

ሕፃናት እንደ አዋቂዎች ሁሉ ደም ግፊት ሊኖራቸው እንደሚችል የሚናገሩት ዶክተሯ ደም ግፊት አብዛኛውን ጊዜ ከልብ እና ከኩላሊት ደም ሥሮች ጋር የተያያዘ ስለሆነ ይህም በአግባቡ ካልተቆጣጠሩት ኩላሊትን እንደሚያደክም ጠቁመዋል፡፡

በአብዛኛው ከቤተሰብ የመወረስ እድል ያለው የኩላሊት ጠጠር ችግርም በተመሳሳይ ሕፃናትን ለኩላሊት ህመም ችግር ሊዳርግ እንደሚችልም ያነሳሉ፡፡

ሕፃናት ለኩላሊት ችግርም ሆነ ለሌላ በሽታ ተጋልጠው እንደሆነ እና እንዳልሆነ በቀላሉ ለመረዳት ወላጆች የልጆችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማለትም የምግብ ፍላጎታቸውን፣ እድገታቸውን፣ጥንካሬያቸውን በማስተዋል መከታተል እንደሚገባም ያስረዳሉ፡፡

ሁልጊዜም ሽንት ሲሸኑ አረፋ ወይም ዝቃጭ ነገር የሚታይ ከሆነ ሽንታቸው ደም መሳይ ወይም እንደ ሻይ ወይም ኮካ መልኩ የመቀየር የመደፍረስ ምልክት ካለው የሕመም ምልክት መሆኑን መረዳት ይቻላል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሕፃኑ በሚሸናበት ወቅት ትንሽ ጠብ አድርጎ ነው ወይስ በደንብ ይሸናል የሚለውን እንዲሁም የሰገራ ድርቀት ካለባቸውም ያምጣል ወይ አያምጥም የሚለውን ባለው አጋጣሚ መከታተል እንደሚገባም ነው ዶክተር ቤዛዬ የጠቆሙት፡፡

በእርግዝና ወቅት ከ 18 እስከ 20 ሣምንት ካለው ጊዜ ጀምሮ በሚደረግ ክትትልም ከሌሎች ከሚታዩ መሰረታዊ አካላት ጋር ኩላሊቶች ያሉበት ሁኔታ በሚገባ መታየት እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡

ሕፃናት ከተወለዱ በኋላ አመጋገባቸውን ማስተካከል ምግባቸውን የተመጣጠነ ማድረግ ውሀ እንዲሁም ንጥረ ነገር ያላቸው ፈሳሾችን መጠቀም ለኩላሊታቸው ጤና በጣም ጠቃሚ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

ኩላሊታቸው ማጣራት ስለማይችል ከአንድ አመት በታች ላሉ ሕፃ ናት ጨው ያለው ምግብ ስለማይሰጥ ከዚህ በፀዳ መልኩ አመጋገባቸውን ማስተካከል እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡

ሕፃናት እንደ ጉንፋን ባሉ ህመሞች በሚያዙበት ጊዜ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና ትኩሳት ሊኖር ስለሚችል ለማስታገስ የሚሰጣቸው መድሃኒት ኩላሊታቸው ላይ ችግር እንዳይፈጥር በባለሙያ ምክር ታግዞ መስጠት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.