Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል በሙስና የተጠረጠሩ አመራሮች በሕግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በሙስና የተጠረጠሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋል መጀመራቸውን የክልሉ ጸረሙስና ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
 
በሐረሪ ክልል የተቋቋመው የፀረ ሙስና ግብረ ሃይል ሰብሳቢ አቶ አዩብ አህመድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በክልሉ በመንግስት ተቋማት ለሙስና እና ለመልካም አስተዳደር መበላሸት ምክንያት የሆኑ ችግሮች ተለይተዋል፡፡
 
በዚህ መሰረትም ግብረ ሃይሉ በዋናነት በመሬት ነክ ጉዳዮች፣ በገቢ፣ በፍትሕ ፣ በፕሮጀክቶች እና ግዢ ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
እስካሁን በተከናወኑ ስራዎች በክልሉ ከመሬት ምዝበራ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ የመሬት ልማት ጽህፈት ቤት አመራሮች፣ መሃንዲሶች እና የፋይናንስ ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
 
ይህን ተከትሎም በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ንብረት የማጣራት እና የማገድ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
 
በሌላ በኩል የሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ በህገ ወጥ መንገድ የተላለፈ ከ17 ሺህ ካሬ በላይ መሬት ታግዶ ወደ መንግስት የመሬት ባንክ ገቢ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
 
ለቀጣይ ስራዎች ስኬት ሲባልም በክልሉ የኢንዱስትሪ መንደርና ከሰዎች ለሰዎች ኮሌጅ ጀርባ ያለ መሬት ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ መታገዱን አቶ አዩብ አስረድተዋል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም ከ16 ሚሊየን ብር ያለአገባብ ሊፈጸም የነበረ የገንዘብ ክፍያ መታገዱን ጠቁመው፥ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለውምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
 
በቀጣይ በሚደርሱ ጥቆማዎች እና በምርመራ ሒደት ላይ በሚገኙ ጉዳዮች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን አስፈላጊውን ማስረጃ በማሰባሰብ በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
 
ሙስናን በተቋቋመው ግብረ ሃይል ብቻ መከላከል አይቻልም ያሉት አቶ አዩብ፥ ማህበረሰቡ ከግል ጥላቻ እና ሀሰተኛ ክስ በጸዳ መልኩ ሙስና የሚፈጽምን ማንኛውንም አመራር እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በተመሳሳይ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ፣ ባንኮች እና ሌሎች ተቋማት በተጠርጣሪዎች ላይ ማስረጃ ለማሰባሰብ በሚደረገው ጥረት ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
 
 
በመላኩ ገድፍ
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.