Fana: At a Speed of Life!

የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ እንደተናገሩት÷ የንግስ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ፖሊስ ቀደም ብሎ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በዚህም የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውስዋል።

በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በዓሉ በድምቅት በሚከበርባቸው በቁልቢና በሐዋሳ አካባቢዎች ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ሁሉ የጸጥታ ጥበቃ ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል፡፡

ህብረተሰቡ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በአቅራቢያቸው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥም ፌደራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.