Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የሚከበሩ በዓላት በተሳካ መልኩ እንዲከበሩ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሚከከበሩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክብረ በዓላት በተሳካ መልኩ እንዲከበሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡

የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በክልሉ ከታኅሣሥ ጀምሮ የሚከናወኑ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክብረ በዓላትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክዋኔዎች ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት ዓይነተኛ ሚናን እንደሚጫወቱ ተገልጿል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሒር ሙሐመድ÷ የልደት በዓል በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ቢከበርም በላሊበላ ከተማ በልዩ ሁኔታ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በጦርነቱና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጎድቶ የነበረውን ቱሪዝም ለማጠናከር የተሻለ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጎንደር የሚከበረውን የጥምቀት በዓል፣ በሰሜን ሸዋ፣ በኢራንቡቲ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል፣ በእንጅባራ የሚከበረውን የአገው ፈረሰኞች በዓል፣ በደብረ ታቦር የሚከበረውን የመርቆርዮስ በዓልና ሌሎችንም በዓላት በደመቀ መልኩ እንዲከበሩ ቢሮው ከአካባቢው አሥተዳደሮችና ማኅበረሰቡ ጋር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በሰከላ የሚከበረውን የግዮን በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው÷ ለሁሉም በዓላት ለሚታደሙት እንግዶች የቱሪዝም ትውውቅ በማድረግ ዘርፉን የማጠናከር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

ቢሮው ከዓመት ወደ ዓመት የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር እየሠራ ነው ያሉት አቶ ጣሒር÷ በተለይ በዓላቱ በጎንደርና በላሊበላ ከተሞች ሲከበሩ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይኖር ከነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።

የዋጋ ንረቱ ጎብኚዎችን ሊጎዳ ስለሚችል አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የእርምት እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

“አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግጁ መሆናቸውንና አሁን ላይ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም መኖሩን መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.