Fana: At a Speed of Life!

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በቀጣዩ የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ በተሞክሮነት ሊቀርብ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በቀጣዩ የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ በተሞክሮነት እንደሚቀርብ በአፍሪካ ሕብረት  የፖለቲካ ፣ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር  አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን  በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአፍሪካ ሕብረት  የፖለቲካ ፣ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር  አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ በውይይ ላይ እንደገለጹት÷ በፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት አህጉሪቱ የራሷን ችግር በራሷ ለመፍታት የያዘችው መርሕ ውጤት እያስመዘገበ ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መሆናቸው ጠቁመው÷ ግጭቱ ተከስቶባቸው በነበሩ የሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነት መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ  መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በግጭቱ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች ዳግም እየጀመሩ መሆናቸውን እና መንግሥት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ሙሉ ቁርጠኝነት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ  የሰላም ስምምነቱ ለሌሎች የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት መልካም  ተምሳሌት መሆኑን አንስተዋል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በቀጣይ በአዲስ አበባ በሚደረገው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በተሞክሮነት እንደሚቀርብም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከመሠረቱ ጀምሮ ለአፍሪካ ሕብረት የሰጠው  ጽኑ አቋም ከፍተኛ አድናቆት እንደሚቸረውም ነው የተናገሩት፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነት እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀምሩ በማድረግ ረገድ የታየው ተግባራዊ ሥራ የሚያስመሰግን መሆኑንም ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.