Fana: At a Speed of Life!

የዓለም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓለም አቀፋዊ ትብብርን በማጠናከር ኮቪድ-19ን ለመታገል የጥምረት ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓለም አቀፋዊ ትብብርን በማጠናከር ኮቪድ-19ን ለመታገል የጥምረት ጥሪ አቀረቡ።

በአሁኑ ሰዓት የኮቪድ-19 በመላው ዓለም በፍጥነት እየተዛመተ ይገኛል ያሉት ፓርቲዎቹ ወረርሽኙ ለመላው የዓለም ህዝብ የጤንነት፣ የዓለም ሰላምና ብልጽግና ተጨባጭ ፈተናዎችን ደቅኗል ብለዋል።

ይህ  እጅግ አስቸጋሪ ፈተና ሁሉም የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ አካላት የተቀናጀ ጥረት በመፍጠር በጋራ ሊዋጉት ይገባል ብለዋል።

የበርካታ ሀገራት ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎችም የህዝባቸውን ደህንነት የመጠበቅ፣ የሀገራቸውን ብልጽግና እና የዓለምን ሰላምና መረጋጋት የማስጠበቅ ያለባቸውን ትልቅ ሃላፊነት ግምት ውስጥ ያስገባ ያሉትን የባለ 10 ነጥብ የጋራ ጥሪ አቅርበዋል።

የብልጽግና ፓርቲም ጥምረቱን በጋራ ያጸደቀና ኮቪድ-19 በሀገራችንና በአፍሪካ የባሰ ጉዳት እንዳያደርስና በጊዜ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ከመደገፍ ባለፈ ዓለም አቀፋዊ ትብብርን በመፍጠር የኮቪድ-19ኝን መስፋፋት ለመግታትና ለመቆጣጠር ብሎም ለማስወገድ የሚሰሩ ስራዎችን እንደሚደግፍ አስታውቋል።

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ሀገራት የቫይረሱን ስርጭት በአግባቡ መቆጣጠር ካልቻሉ በሰዎች ጤንነት፣ ደህንነት፣ ማህበራዊ ህይወት እና በሀገራት ግኑኝነት እና ትብብር ላይ የከፋ ጉዳት እንደሚደርስ አስታውቀዋል።

በመሆኑም ሀገራት የዜጎቻቸውን ጤንነት ያሰቀደመ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ የሚመጣውን ጉዳት እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዜጎችም በሀላፊነት መንፈስ የቫይረሱን ስርጭት የመከላከል ጥረቱን እንዲያግዙም ነው ያሳሰቡት።

ሀገራት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ አካሄድ እንዲከተሉ በመጠየቅ በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ለአነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ተቋማት ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

ቫይረሱ አንድን ሀገር ለይቶ የማያጠቃ መሆኑን በመገንዘብም ሀገራት በፍፁም ሰብዓዊነት ቫይረሱን እንዲዋጉም ነው የጠየቁት።

ቫይረሱ ቀድሞ ተከስቶባቸው መቆጣጠር የቻሉት ቻይናን የመሰሉ ሀገራት  በግልፅነት ተገቢውን መረጃ በመስጠት ልምዳቸውን በማካፈል የቫይረሱን ወረርሽኝ የመግታቱን ጥረት እንዲያግዙም አሳስበዋል።

የቡድን 20 ሀገራት ለቫይረሱ ህክምናን ለማግኘት የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለመደገፍ ያወጡትን መግለጫ ያደነቁት ፓርቲዎቹ፥ እነዚህ ሀገራት በማደግ ላይ የሚገኙትን ሀገራት በቁሳቁስ እና በቴክኒክ እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

ፓርቲዎቹ ይህ ወረርሽኝ ካለፈ በኋላ የሰው ልጅ የበለጠ ጠንክሮ ሰብዓዊነት እንደሚያብብ እምነታቸውን ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.