Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለተጨማሪ 1 ሺህ 559 ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለተጨማሪ ለ1 ሺህ 559 ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን በዛሬው እለት አስታውቋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በጉዳዩ ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎቹ በየፖሊስ ጣቢያ የነበሩ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ መረጃቸው በወቅቱ ለውሳኔ በሚመች ሁኔታ ተጣርቶ ያልቀረበ እንዲሁም የፌደራል ታራሚዎች ሆነው በየክልሉ የነበሩ ታራሚዎች ናቸው።

እነዚህ ታራሚዎች በወቅቱ ከነበረው አጣዳፊነት አንፃር ከዚህ ቀደም ይቅርታ የተደረገላቸው ውስጥ ማካተት ሳይቻል ቀርቶ እንደነበረም ገልፀዋል።

ለ1 ሺህ 559 ታራሚዎች ይቅርታ የተደረገውም የይቅርታ ቦርዱ ማረሚያ ቤት አጣርቶ ባቀረበለት መረጃ መሰረት በማጣራት ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በማቅረብ በተላለፈ የይቅርታ ውሳኔ መሆኑን አስታውቅዋል።

በዚህም በአጠቃላይ ለ1 ሺህ 559 ታራሚዎች ይቅርታ የተደረገ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 511 ወንዶች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ 48 ሴቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በማረሚያ ቤቶች ለመከላከል ይቻል ዘንድ ከዚህ ቀደምም 4 ሺህ 11 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ እንደተደረገ መግለፁ ይታወሳል።
የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት የህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።

ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች በሚያጋጥሙ ጊዜ የሚተላለፉ መመሪያዎች እና ውሳኔዎች ህግ ናቸው ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ እነዚህን ተላልፎ መገኘት ከቀላል እስራት እስከ እድሜ ልክ እስራት ሊያቅሰጡ ይችላሉም ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ርቀትን አለመጠበቅ፣ ለቫይረሱ የሚያጋጥሉ ተግባራትን መፈፀም፣ የወጡ መመሪያዎችን በተለያዩ መንገዶች መጣስ፣ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ መንገደኞች የተቀመጠውን የአስገዳጅ የለይቶ መቆያ መመሪያ መጣስ፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት፣ በአቋራጭ ለመክበር ምርት መደበቅና ዋጋ መጨመር የሚፈጽሙ አካላት ላይ ተገቢው የህግ ማስከበር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞም ከ15 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዱን የገለጹት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፥ ከ424 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በህግ ቁጥጥር ስው ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል ብለዋል።

የለይቶ ማቆያ (ኳራንቲን) ህግን ካለማክበር ጋር በተያያዘ የመጡ ጥቆማዎችን መኖራቸውንም በማንሳት፤ ተገቢው የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በእምነት ተቋማት አካባቢም በተመሳሳይ ህግ እና መመሪያዎችን በማስተማር ዙሪያ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህጓ፥ ነገር ግን በተቀመጠው አሰራርና መመሪያ ሁኔታ የማይተገበር ከሆነ ህግ የማስከበር ስራ ይሰራል ብለዋል።

ከለይቆ ማቆያ (ኳራንቲን) እና የህክምና ስፍራዎችን የመለየትና ግብዓት የሟሟላት ስራም ተጠናክቶ መቀጠሉን በማንሳት፥ ከለይቶማቆያና የሕክምና ክትትል ማድረጊያ አንጻር ከ80 ሺህ በላይ ሰዎችን ማስተናድ የሚችሉ 180 ቦታዎች መለየታቸውም አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.