Fana: At a Speed of Life!

40ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር የፊታችን እሑድ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 40ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር  የፊታችን እሑድ በሱሉልታ ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ።

የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ÷ በመጪው እሑድ በሚካሄደው 40ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር ከ1 ሺህ 29 በላይ አትሌቶች ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ውድድሩ ከጃንሜዳ ወደ ሱሉልታ የቦታ ለውጥ የተደረገው ጃንሜዳ ኮቪድ-19 በገባበት ወቅት የአትክልት መሸጫ ሥፍራ ሆኖ ሲያገለግል በመቆየቱ ለውድድር አመቺ ባለመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይም ጃንሜዳ ለመገበያያ እንዲያመች ድንጋይና ጠጠር ተደልድሎበት በመቆየቱ አሁንም ላይ ለውድድር አመቺ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።

የፌዴሬሽኑ የውድድርና ተሳትፎ የሥራ ሂደት መሪ አስፋው ዳኜ÷ውድድሩ በ10 ኪሎ ሜትር በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች፣ በ8 ኪሎ ሜትር በወጣት ወንዶች፣ በ6 ኪሎ ሜትር በወጣት ሴቶች፣ በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ሪሌና በአንጋፋ አትሌቶች መካከል የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው ለሚያጠናቅቁ ተወዳዳሪዎች የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ይሰጣቸዋል ተብሏል።

በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች ውድድር ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ለሚያጠናቅቁ ለእያንዳንዳቸው እንደ የደረጃቸው ከ50 ሺህ ብር እስከ 14 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ስለመዘጋጀቱም ተጠቅሷል።

በወጣት ወንዶችና ሴቶችም ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁም ለእያንዳንዳቸው እንደ የደረጃቸው ከ40 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በድብልቅ ሪሌ እና ለአንጋፋ አትሌቶችም የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን÷በሻምፒዮናው አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በአውስትራሊያ በሚካሄደው 44ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ይካፈላሉ ተብሏል፡፡

በሩጫው እንዲሳተፉ ጥሪ ከተደረገላቸው ሀገራት መካከል የሱዳን አትሌቶች እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ መስጠታቸው ተገልጿል።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.