Fana: At a Speed of Life!

ህዳሴ ግድብን ዓለም አቀፍ ስጋት ከሆነው የኮሮናቫይረስ ውጪ ከግስጋሴው የሚገታው ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደማይኖር ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አሁን ዓለም አቀፍ ስጋት ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ውጪ ከግስጋሴው የሚገታው ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደማይኖር ተገለፀ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 9ኛ ዓመት በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፥ ኢትዮጵያ የምታከናውነው ግድብ ግንባታ ለሌሎች የውጭ ሀገራት ተፅዕኖና ለየትኛውም የሀገር ውስጥ ችግሮች ሳይበገር ይቀጥላል ብለዋል።

በመጪው ክረምት ሐምሌ ወርም ግድቡ 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ለመያዝ የሚያስችለው ስራ እየተከናወነ ይገኛል እንደሚገኝም አንስተዋል።

ለዚህም ህብረተሰቡ ይህንን ሀገራዊ ዕቅድ ከማሳካት ሊያግደው ከሚችለው ኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት እራሱን በመጠበቅ፤ ተሳትፎውን ማጠናከር ይገባዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው፥ አሁን ያለው ወቅታዊ የአፈጻጸም ሁኔታ ግድቡ በክረምቱ ወቅት ሐምሌ ወር ውሃ ለመያዝ በሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ግድቡን በታቀደለት ጊዜ ውሃ መሙላት ባይቻል ግን ሀገሪቱ ግድቡ በአንድ ዓመት ያመነጨው ከነበረው ሃይል 1 ቢሊየን ዩሮ ገቢ እንደምታጣ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ክንውን 86 በመቶና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው 44 ከመቶ የደረሰ ሲሆን በአጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 72 ነጥብ 4 በመቶ አፈጻጸም ላይ መሆኑን የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገልፀዋል።

የህዝባዊ ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው ያሉት የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ፥ ባለፉት 8 ወራት 405 ገጥብ 9 ሚሊየን ብር በቦንድ ግዢና በስጦታ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

እስካሁንም በጥቅሉ 13 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ዜጎች መገኘቱን ገልፀዋል።

በሶዶ ለማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.