Fana: At a Speed of Life!

ሰሜን ኮሪያ ወደ ጃፓን ባህር ክልል ሚሳኤል ማስወንጨፏ ተሰማ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ ወደ ጃፓን ባህር ክልል ሚሳኤል ማስወንጨፏን የጃፓን ወታደራዊ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ከመዲናዋ ፒዮንግያንግ በደቡባዊ አቅጣጫ ከምትገኘው ህዋንግሄ ክልል የተወነጨፉት ሚሳኤሎች የአጭር ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎች መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

ፒዮንግያንግ አሁን ሚሳኤል ያስወነጨፈችበት አካባቢም ለዚህ ተግባር ሲውል ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።

የተወነጨፉት ሚሳኤሎች እያንዳንዳቸው በጃፓን ባህር ክልል 350 ኪሎ ሜትር ርቅት መጓዛቸውንም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።

የአሁኑ የሚሳኤል ሙከራ ደቡብ ኮሪያ ከትናንት በስቲያ ሮኬት ማስወንጨፏን ተከትሎ የተሰጠ ምላሽ ነው መባሉን ምንጮችን ጠቅሶ አር ቲ አስነብቧል።

ሴኡል ሮኬቱ በህዋ ላይ ለምትገነባውና የሰሜን ኮሪያን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመቃኘት ለምትጠቀምበት አገልግሎት የሚውል ነው ብላለች።

ሰሜን ኮሪያ በፈረንጆቹ 2022 የአመቱ የመጨረሻ የሆነውን የዛሬውን የሚሳኤል ሙከራ ጨምሮ በርካታ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ አድርጋለች።

በአመቱ ወደ 70 የሚጠጉ የአጭር ርቀት ሙከራዎችን እንዲሁም ሶስት ክሩዝ ሚሳኤል ማስወንጨፏን የደቡብ ኮሪያው ዩንሃፕ ዘግቧል።

ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በዚህ አመት ከአሜሪካ ጋር ተደጋጋሚ ወታደራዊ ልምምዶች ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.