Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ ለድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በገቢዎች ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽኅፈት ቤት ለታማኝ ግብር ከፋዮቹ የዕውቅና ሽልማት ሰጠ።

ጽኅፈት ቤቱ በ 2014 በጀት ዓመት በታማኝነት ግብራቸውን አሳውቀው ለከፈሉ የድሬዳዋና የሐረሪ ክልል የፌደራል ግብር ከፋይ ለሆኑ 23 ታማኝ ግብር ከፋዮች ነው የዕውቅና ሽልማት የሰጠው፡፡

በእውቅና ሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ ተገኝተዋል፡፡

ወ/ሮ መሠረት ÷ ለታማኝ ግብር ከፋዮቹ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ከሰጡ በኋላ እንደተናገሩት ሀገራዊ ወጪን በራስ መሸፈን የሚለውን ሀገራዊ የገቢ ዘርፍ ተልዕኮ ለማሣካት ግንባር ቀደም ግብርን በታማኝነት የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ለሀገር ልማት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል።

በ 2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ወራትም በፌደራል ደረጃ 195 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ግብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ48 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ነው የጠቆሙት፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ ታማኝ ግብር ከፋዮቹ ሌሎችንም በማስተማር ረገድ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ነው ያሳሰቡት፡፡

በገቢዎች ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አትሃም መሐመድ በበኩላቸው ÷ በ2014 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በመሠብሰብ የዕቅዱን 123 በመቶ ማሣካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ለዕቅድ አፈጻጸሙም ስኬታማነት የታማኝ ግብር ከፋዮች አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ግብር ከፋዮቹ ከፕላቲንየም ጀምሮ እስከ ሠርተፍኬት ድረስ ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋልም ነው የተባለው፡፡

በዕውቅና እና ሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለ90 ቀናት የቆየ በታክስ አስተዳደር፣ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆኑ ታክሶች ላይ በተዘጋጁ 13 ሞጁሎች ሥስልጠና የተከታተሉ 90 ግብር ከፋዮች መመረቃቸውም ታውቋል፡፡

በተሾመ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.