Fana: At a Speed of Life!

ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅም አውለዋል የተባሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሠራተኞች ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሲሚንቶ ግዢ ጋር በተያያዘ ከ30 ሚሊየን በላይ ብር ለግል ጥቅም አውለዋል የተባሉ አራት የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ሠራተኞች ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ።

ተከሳሾቹ÷ 1ኛ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ምክትል ዳይሬክተር ተስፋዬ ደሜ፣ 2ኛ በተቋሙ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ግዢ ዋና ክፍል ኃላፊ አሸናፊ ተስፋዬ፣ 3ኛ በተቋሙ የግዢ ባለሙያ ቱጅባ ቀልቤሳ እና 4ኛ ሙስጠፋ ሙሳ ናቸው፡፡

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ተቋም የግዢ ፍላጎት ሳይኖረው ትዕዛዝ ባልተሰጠበት እና ከተቋሙ ዕውቅና ውጪ የግዢ ባለሙያ ሆነው ሲሠሩ÷ በጥቅም በመመሳጠር በ2013 እና 2014 ዓ.ም በተለያዩ ቀናት ለተቋሙ ነው በሚል ከሁለት ፋብሪካዎች የገዙትን 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ምርት ለግለሰቦች በመሸጥ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ጠቅሷል፡፡

በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ስልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል በታኅሣሥ 3 ቀን በነበረ ቀጠሮ መከሰሳቸው ይታወሳል።

ተከሳሾቹ ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

ተከሳሾቹ ባለፈው ቀጠሮ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የሰጡትን የእምነት ክህደት ቃል ተከትሎ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመጠባበቅ የተሰየመው ችሎቱ÷ በፍርድ ቤቱ አስተዳደር በኩል ለምስክሮች መጥሪያ ባለመውጣቱ ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን በስልክ ጥሪ በማድረግ ለነገ በይደር እንደሚያቀርባቸው ለችሎቱ መግለጹን ተከትሎ ችሎቱም ምስክሮችን ለመስማት በይደር ቀጠሮ ይዟል።

ተከሳሾቹ በጤና ችግር እና ደኅንነት ስጋት ምክንያት በፌደራል ፖሊስ ጊዜያዊ ማቆያ አባሳሙኤል እንድንቆይ ይፈቀድልን ሲሉ ችሎቱን ቢጠይቁም÷ ዐቃቤ ሕግ አባሳሙኤል ጊዜያዊ የፌደራል ፖሊስ የተጠርጣሪዎች ማረፊያ እንጂ የመደበኛ የተከሳሾች መኖሪያ እንዳልሆነ በማብራራት ተከሳሾቹ የጤና ችግር እንዳለባቸው በማስረጃ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በጊዜያዊ ማቆያ ለመቆየት ያቀረቡት አቤቱታ ተገቢነት የለውም ሲል ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ በማስረጃ የተደገፈ አለመሆኑን ተከትሎ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ አዟል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.