Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የምሁራን የውይይት መድረኮች እየተካሔዱ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ፣ አርሲ፣ ሰላሌ ፣ ደብረ ብርሃን፣ በወራቤ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች “የምሁራን ሚና ለሀገር ግንባታ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የምሁራን ውይይት እየተካሔደ ነው፡፡

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው ውይይት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ምህረት ደበበ ፣የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ፣ የሁሉም ኮሌጆች የካውንስል አባላት መምህራንና የአስተዳደር ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

ውይይቱን የሚመሩት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ሲሆኑ መድረኩ ለአራት ቀናት እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡

በአርሲ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ዓላማ እንደሀገር ያሉ አቅሞችን አሟጦ ለመጠቀምና አሁን ላይ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን ለመቅረፍ ምሁራን በሙያቸው መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ማድረግ መሆኑ ተጠቅሷል።

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቶላ በሪሶ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተገኙ ለውጦችን ለመድረኩ ተካፋዮች አቅርበዋል፡፡

የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስም የምሁራን ሚና የላቀ በመሆኑ በሙያቸው መደገፍ፣ ያሉት ችግሮች ደግሞ ጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ እንዲያገኙ ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው አዝገንዘበዋል።

ውይይቱ ለሁለት ቀን እንደሚካሄድም ታውቋል።

በተመሳሳይ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የምክክር መድረኩ እየተካሄደ ሲሆን÷ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር እንዲሁም የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ መኩሪያ ኃይሌ መነሻ የሚሆን ሰነድ አቅርበው ውይይት እየተካሄደበት ነው፡፡

እንዲሁም ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ “በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና” በሚል ርዕስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ መድረኩ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የመወያያ መነሻ ሰነዱን ለውይይት አቅርበዋል፡፡

የውይይቱ ዓላማም ምሁራን የምርምር ስራ በመስራት፣ ትችት በማቅረብና የመፍትሄ አቅጣጫ በማመላከት ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም ምሁራንን በማሳተፍ ጠቃሚ ግብዓቶችን በመውሰድ፣ የተሻለችና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ተገቢ በመሆኑ መድረኩ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

በወራቤ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ÷ የሀገረ-መንግስት ግንባታና ሀገራዊ እንዲሁም ዓለማቀፋዊ ፈተናዎችን በሰፊው ያብራሩ ሲሆን ምሁራን በሀገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን አዎንታዊ ድርሻ መጫወት እንዳለባቸው አንስተዋል።

አክለውም ምሁራን በብሄራዊ አገልግሎት፣ በበጎ ፈቃድ እና ማኅበራዊ ኃላፊነት በመሳተፍ የትውልድ ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

እንዲሁም በጅማ ዩኒቨርሲቲ “የምሁራን ሚና ለሀገር ግንባታ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የምሁራን ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በኦሊያድ በዳኔና ዮናታን ብርሃኑ፤ ተጨማሪ መረጃ ከአዲስ አበባ ፣ሰላሌ ፣ ደብረ ብርሃን እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.