Fana: At a Speed of Life!

ከአገልግሎት ውጪ በሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች ፣ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪች ሽያጭ ላይ የዋጋ ማሻሻያ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአገልግሎት ውጪ በሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ሽያጭ ላይ የዋጋ ማሻሻያ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የብረት አምራች ፋብሪካዎች የግብአት እጥረትን ለመቅረፍ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የማዕድን ሚኒስቴር በጋራ በተለያዩ የፌደራል መንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የሚገኙ ቁርጥራጭ ብረታብረቶች፣ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ለብረት አምራቾች የገንዘብ ሚኒስቴር በሚወስነው ዋጋና የማዕድን ሚኒስቴር በሚደለድለው የብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ኮታ መሰረት በሽያጭ እንዲቀርቡ ተወስኖ ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል፡፡

እስከ አሁን ድረስም የተለያዩ ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ቁርጥራጭ ብረቶቹን እየወሰዱ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ከአፈጻጸም ጋር በተያያዘም ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎቹ ከትራንስፖርትና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ጋር በተያያዘ የዋጋ ማሻሻያ እንዲደረግላቸው ለማዕድን ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት ማግኘታቸው ተጠቁሟል፡፡

የመንግስት ዋነኛ አላማ የሽያጩ ዋና መነሻ ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥሬ ዕቃ እንዲያገኙ፣ ምርታማነታቸው እንዲጨምር እንዲሁም መንግስት ያወጣው የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት በመሆኑ የአምራች ፋብሪካዎቹን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የዋጋ እና ሌሎች ወጪዎች ማሻሻያ ተደርጓል፡፡

በዚህም መሰረት ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ከአዲስ አበባ በ100 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ውስጥ ከሚገኙ መስሪያ ቤቶች ውጭ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ሲገዙ በሚከተለው የዋጋ ተመን የሚገዙ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

“ስቲል ቁርጥራጭ ብረት” የቀድሞ የአንድ ኪሎ መሸጫ ዋጋው 64 ብር የነበረ ሲሆን የተሻሻለው መሸጫ ደግሞ 48 ብር እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ካስት አይረን ቀድሞ በኪሎ በ51 ብር ከ75 ሲሸጥ የነበረ ሲሆን ዋጋው ተሻሽሎ በኪሎ 35 ብር የሚሸጥ ይሆናልም ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም “ውጋጅ ተሽከርካሪ እና ማሽነሪዎች” በኪሎ 51 ብር ከ25 ሲሸጡ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በኪሎ 39 ብር እንዲሸጡ የዋጋ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል፡፡

“አልሙኒየም ቁርጥራጭ”ም በኪሎ ከ120 ወደ 90 ብር እንዲሁም ያገለገሉ የተሸከርካሪ/ማሽነሪ መለዋወጫዎች ዋጋ በኪሎ ከ51 ብር ከ25 ወደ 39 ብር እንዲሻሻሉ ተመን የተቆረጠባቸው ናቸው፡፡

አቅላጭ ፋብሪካዎች ከአዲስ አበባ ከ100 ኪ.ሜ ርቀት ሬዲየስ ውጪ ከሚገኙ መስሪያ ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች ፣ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ሲገዙ ደግሞ ከላይ የተጠቀሰው የዋጋ ማሻሻያ እንደተጠበቀ ሆኖ ከታች የተዘረዘሩት ወጪዎች ተቀናሽ ተደርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት አንድ ኪሎ “ቁርጥራጭ ብረት” ለመቁረጥ፣ ለመለየት፣ ለመሰብሰብ ብር 5.80 /አምስት ብር ከ80/100/

 አንድ ኪሎ የቁርጥራጭ እና ውጋጅ  ብረት ለማስጫን ብር 2.50 /ሁለት ብር ከ50/100/

 ለትራንስፖርት ለአንድ ኪሎ ሜትር ብር 0.009534 ተቀናሽ እንደሚደረግ መወሰኑንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክል፡፡

ስለሆነም አዲስ የተሻሻለው ቁርጥራጭ እና ውጋጅ የመሸጫ ዋጋ መሰረትም የማእድን ሚኒስቴር ለሚመድባቸው ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ብቻ ያለተጨማሪ እሴት ታክስ ያለ ጨረታ እንዲሸጥ መወሰኑ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በጨረታ ሂደት ላይ የሚገኝ የየትኛውም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወይም የመንግሥት ተቋማት የጨረታ ሂደቱ ተቋርጦ አሁን መንግስት ስራ ላይ እንዲውል በወሰነው መሰረት ይከናወናል ነው የተባለው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.