Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ፀረ ሙስና ኮሚቴ 127 ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ ጥቆማዎች ማሰባሰቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አደረጃጀት የተቋቋመው የፀረ ሙስና ኮሚቴ 127 ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ ጥቆማዎችን ማሰባሰቡን አስታወቀ፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመውን የፀረ ሙስና ኮሚቴ ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀረ ሙስና ኮሚቴ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማቋቋማቸው ይታወቃል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተቋቋመው የፀረ ሙስና ኮሚቴ ሁለት ንዑሳን ኮሚቴዎች ያሉት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በሰጡት መግለጫ ÷ ንዑሳን ኮሚቴ ተደርገው የተደራጁት የህግና የምርመራ ንዑስ ኮሚቴና የጥቆማና መረጃ ንዑስ ኮሚቴ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

የተጠቀሱት ሁለት ንዑሳን ኮሚቴዎችን አደራጅቶ በይፋ ተግባራዊ የሥራ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረ ግዜ አንስቶ 127 ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ የሙስና ጥቆማዎችን ከሕዝብ ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

ከ127 ከሕዝብ የተሰበሰቡ ጥቆማዎች መካከል 64 የሚሆኑትን በፍጥነት በመለየትና የክስ መዝገብ በማደራጀት ለሕግና ምርመራ ንዑስ ኮሚቴ መመራቱን ጨምሮ 37 ጥቆማዎች ላይ በቂ መረጃ በማሰባሰብ የክስ መዝገብ የማደራጀት ሥራ መሰራት መቻሉንም አንስተዋል፡፡

በቀሪዎቹ ከሕዝብ የተሰበሰቡ የሙስና ጥቆማዎች ላይም መረጃና ማስረጃ እንዲሁም የክስ መዝገብ የማደራጀት ስራ በዘላቂነት በንዑሳን ኮሚቴዎች በኩል እየተከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

አጠቃላይ መረጃ የማሰባሰብና የክስ መዝገብ የማደራጀት ስራዎች ከፌደራል ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ጋር በቅንጅት የሚከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

እየተደረገ ባለው መረጃ የማሰባሰብ ሂደት እስካሁን እየመጡ ያሉ ጥቆማዎች የሚበረታቱና የተጀመረውን የፀረ ሙስና ትግል የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.