Fana: At a Speed of Life!

ተቋሙ የመልካም አሥተዳደር አፈፃፀም ተግባር ለመከታተል የሚያሥችል ሥራ ሊሠራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመልካም አሥተዳደር አፈፃፀም ተግባር ለመከታተል የሚያሥችል ሥራ ሊሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል፡፡

ተቋሙ እንዳለው ፥ የመንግሥት አሥፈፃሚ አካላትን የመልካም አሥተዳደር ተግባር መለካት፣በደረጃ መለየት እና እውቅና መሥጠት የመልካም አሥተዳደርን ለማሥፈን ወሣኝ ሥራ ሆኖ ተገኝቷል።

በፌዴራል ደረጃ ካሉ 22 ሚኒሥቴር መሥሪያ ቤቶች ውሥጥ በ 15ቱ ላይ ሥራው እንደሚጀመርም ነው የተገለፀው።

በቀጣይ በሁሉም የፌዴራል እና ክልል እንዲሁም ከተማ አሥተዳደሮች ውሥጥ በሚገኙ የመንግሥት አሥፈፃሚ አካላት ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግም ተጠቁሟል፡፡

በተሠጠው ሥልጣን መሠረት የተቋማትን የመልካም አሥተዳደር አፈፃፀም የሚከታተለው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ÷ ይህም አሥተዳደራዊ በደልን ለመከላከል ያሥችለዋል ተብሏል።

በተጨማሪም ነባር ህጎችን ለማሻሻል እና አዳዲሥ አሠራሮችን ለመዘርጋትም ክትትሉ አሥፈላጊ እንደሆነም ነው የተነሳው።

ወደ ተግባር ከመገባቱ በፊትም የተለያዩ ዓለማቀፋዊ እውቅና ያላቸው ተሞክሮዎች ተወሥደው መመሪያ መዘጋጀቱንና ለተቋማት ባለ ሙያዎችና አመራሮች ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉንም ነው ተቋሙ ያሥታወቀው።

ቅድሚያ መለካት ያለባቸው የፌዴራል ሚኒሥቴር መሥሪያ ቤቶችም እንደተለዩ ተገልጿል።

በሜሮን ሙሉጌታ እና ሠሎሞን ይታየው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.