Fana: At a Speed of Life!

ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማዳረስ በትኩረት እየተሰራ ነው – የአማራ ክልል

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የገበያ ያለመረጋጋት እንዳይከሰት ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማዳረስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ፋንታው ፈጠነ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ለዚህም የገበያ ልማት ቢሮው የክልሉ ነዋሪ በተለይ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በአቅራቢያው እንዲገኝ የማድረግ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

እንደ ምክትል ኃላፊው እስካሁን 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት የተሰራጨ ሲሆን፥ 1ነጥብ 9 ሚሊየን ሊትሩ ደግሞ በስርጭት ሂደት ላይ ነው።

በተጨማሪም፥ 7 ሚሊየን ሊትር ዘይት ደግሞ ፊቬላ ዘይት ፋብሪካ በራሱ ተነሳሽነት ከአከፋፋዮች ጋር በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጡ በመነጋገር ወደ ተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሰራጭ እገዛ ዕያደረገ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡

በዚህም በባህርዳር ከተማ 5 ሊትር ፊቬላ ፈሳሽ ዘይት በ870 ብር እየተሸጠ እንደሆነ አቶ ፋንታው አንስተዋል፡፡

ከስኳር ምርት ጋር በተያያዘም ክልሉ ከተያዘለት 115 ሺህ ኩንታል ስኳር ኮታ ሩብ ያህሉን ለማሰራጨት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለእርድ የሚቀርቡ የእንስሳት ተዋጽዎችን በተመለከተም በእንስሳት መሸጫ ማዕከላት ገብተው ጥራታቸው እና ዋጋቸው ተመጣጣኝ መሆኑ ተረጋግጦ ለእርድ የሚቀርቡበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት ፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም የስጋ እና የእንቁላል አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በአመለወርቅ  ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.