Fana: At a Speed of Life!

11 የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በሀሰተኛ ሰነድ ሸጠው ገንዘቡን በመከፋፈል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 11 የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በሀሰተኛ ሰነድ ለልማት ተነሺ በሚል ሸጠው ገንዘቡን ሸጠው ገንዘቡን ተከፋፍለዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ፡፡

ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ከተከሳሾቹ መካከል 1ኛ የቀድሞ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የአስተዳደርና ፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተርና የዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተክሉ ቤያሞን 2ኛ የቀድሞ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የቤት ማስተላለፍና የግብዓት ማምረቻ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ወ/ሮ ፀዳለ መኮንን፣ 3ኛ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በመንግስት ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የልማት ተነሺዎች ክትትል ቡድን መሪ ሌሊሳ ጓሹ እና 4ኛ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በመንግስት ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የልማት ተነሺዎች ክትትል ከፍተኛ ባለሙያ የነበሩት በሪሳ ቃሶ ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም 5ኛ ተከሳሽ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ቤት ማስተላለፍና አስተዳደር ሲኒዬር ባለሙያ ተስፋማርያም ፍሰሃ፣ 6ኛ የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የቤቶች ልማት ተነሺዎች ቤት ማስተላለፍ ባለሙያ፣ 7ኛ የቀድሞ ባለስልጣን የነበሩ አሁን በግል ስራ ላይ ተሰማርተዋል የተባሉት አቶ ውብሸት በላይነህ፣ 8ኛ ተከሳሽ የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን የቤቶች ፋይናንስና ማስተላለፍ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አራጌ እሸቴ፣ 9ኛ ተከሳሽ በድለላ ስራ ተሰማርተዋል የተባሉት አንመው ጸጋዬ እና በተመሳሳይ ደላላ ናቸው የተባሉት 10ኛ ተከሳሽ እንዳልክ ንጉሴ ናቸው፡፡

ቀሪዎቹ ደግሞ በሀሰተኛ ማስረጃ ያለአግባብ በኮዬ ፈጬ ሳይት የልማት ተነሺ በሚል ኮንዶሚኒዬም በስማቸው ወስደዋል ተብለው በክስ ዝርዝሩ የተጠቀሱ ከ11ኛ እስከ 19ኛ ተራ ቁጥር ተከሳሾችም በክሱ ይገኙበታል።

ክሱ እንደሚያመላክተው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱትና 8ኛ ተከሳሽ በመንግስት የስራ ኃላፊነት ተመድበው ሲሰሩ በ2012 ዓ/ም በተለያዩ ወሮችና ቀናቶች በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በተለምዶ ዳትሰን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የልማት ተነሺ ያልሆኑ ከ11ኛ እስከ 19ኛ ተራ ቁጥር የተዘረረዘሩ ተከሳሾችን የልማት ተነሺ ናቸው በማለት በ7ኛ ተከሳሽ ሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጅነት 11 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የዕጣ ዋጋው ከ314 ሺህ እስከ 440 ሺህ ብር በላይ የሆኑ ባለሁለትና ባለሶስት መኝታ ቤቶችን በተጭበረበረ መንገድ በመስጠትና ቤቶቹን ያለአግባብ ወስደዋል የተባሉ ተከሳሾች የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ በክሱ ተዘርዝሯል።

እንደ አጠቃላይ የዕጣ ዋጋው ከ3 ሚሊየን 666 ሺህ ብር በላይ የሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የልማት ተነሺ ላልሆኑት ግለሰቦች ቤቱን በመሸጥ ገንዘቡን በመከፋፈል ህገወጥ ጥቅም አግኝተውበታል ሲል ዓቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

በዚህም አጠቃላይ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ ከ3ኛ እስከ 19ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በሙስና ወንጀል የተገኘውን የመንግስት ሀብት ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ አስተላላፊና ተቀባይ በመሆን ገንዘቡን ተጠቅመዋል ሲል ዓቃቤ ህግ በክሱ ዘርዝሯል።

ከ19 ተከሳሾች ውስጥ አንደኛ እና 2ኛ ተከሳሽን ጨምሮ አጠቃላይ 7 ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ውለው ዛሬ ችሎት የቀረቡ ቢሆንም በዳኛ አለመሟላት ምክንያት ክሱን ለመመልከት በይደር ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.