Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የሚጸናው በህዝቦቿ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ላይ ነው- ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
በመልዕክታቸውም የእየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትርጉሙ የላቀ ነው፤ጨለማ፣ በደልና የሞት ጥላ ተሽረው ብሩህ ተስፋ፣ ነጻነት ፣ ፍቅርና ለሰው ልጆች ሁሉ ዘላለማዊ ሰላም የተገኘበት አዲስ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
 
በልደቱ ያገኘነው ሰላም፣ ነጻነት፣ ብርሃንና ፍቅር ዋጋ የተከፈለበት፤ ሞትን በመወለዱ ያሸነፈበት መሆኑ ይታመናል ሲሉም ገልጸዋል።
 
በመወለዱ ያገኘነው ነጻነትና ሰላም እንደመሆኑ እንደ ሀገር ከዚህም ከዚያም የሚስተዋሉ ችግሮችን ከቂምና በቀል ተላቀን በውይይትና በመነጋገር ቀርፈን የአገራችን ሰላምና አንድነት ማረጋገጥ ይኖርብናል ነው ያሉት።
 
የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የሚጸናው በህዝቦቿ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ላይ ነው፤ ያለፈተና ድል፣ ያለጽናት አሸናፊነት አይታሰብም ብለዋል።
 
ፈተናዎቻችን ሁሉ በአሸናፊነት የምንሻገረው ግን ተነጣጥለን ሳይሆን በመተሳሰብ በአንድነት መቆም ስንችል መሆኑን መረዳት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የሚገነባው እንደሀገር በጋራ በምናደርገው ውይይት ላይ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው ብለዋል።
 
በጋራ ካልተወያየንና ካልተግባባን ችግሮቻችንን በዘላቂነት መፍታት አንችልም፤ጠላቶቻችን ብዙና ተለዋጭ ናቸው። የጠላቶቻችን ተለዋዋጭ ሴራ በማክሸፍ የህዝባችንን ሰላም የምናረጋግጠው በመደማመጥ አንድ ስንሆን ነው ሲሉ አስረድተዋል።
 
ስለሆነም ከምንጊዜም በላይ አንድ ሁነን ሀገራችን በጋራ እናጽና ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
 
ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ለመላው የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የአንድነት እንዲሆንም በራሳቸው እና በክልሉ መንግሥት ስም ተመኝተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.