Fana: At a Speed of Life!

ልዩነቶቻችን የውበታችን መገለጫዎች እንጂ በጥላቻ ለመተያያና መገዳደያ ሰበብ ልናደርጋቸው አይገባም- አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያውያን የሆንን ሁሉ የብዝኃ ሃይማኖት ወይም እምነቶች፣ የብዝኃ ቋንቋ፣ የብዝኃ ባሕልና አመለካከት ባለቤቶች ነን ሲሉ አውስተዋል።
 
ልዩነቶቻችን የውበታችንና የድምቀታችን መገለጫዎች እንጂ በጥላቻ ለመተያያና አለፍ ሲልም ለመገዳደያ ሰበብ ልናደርጋቸው አይገባም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
 
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል ፡-
 
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡
 
በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ዕለት የመላእክት ወገን፣ የእንስሳት ወገንና የሰው ወገን በጠባብ በረት ውስጥ ሕብር ፈጥረው፣ በመካከላቸው ያለውን ልዩነታቸውን አክብረው ለአንድ ዓላማ ተሰልፈው እንደነበር እንመለከታለን፡፡
 
በዚያች ዕለት ቋንቋ የልዩነት አጥር ሆኖ ከጋራ ተልእኳቸው አላደናቀፋቸውም፤ ልዩ የሆነው ተፈጣሯዊ ባህሪያቸውም መሰናክል ሆኖ በአንድነት ከመቆም አላገዳቸውም፡፡ ልዩነታቸው ለቤተልሔም ከተማ ድምቀት፤ አንድነታቸው ደግሞ ለጋራ ዓላማቸው ጉልበት፣ ብዝኃነታቸውም ውበት ሆኗቸዋል እንጂ።
 
ይህ ክስተት ለእኛ ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ትልቅ ቁምነገር ያስተምረናል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን የሆንን ሁሉ የብዝኃ ሃይማኖት ወይም እምነቶች፣ የብዝኃ ቋንቋ፣ የብዝኃ ባሕልና አመለካከት ባለቤቶች ነን። ልዩነቶቻችን የውበታችንና የድምቀታችን መገለጫዎች እንጂ በጥላቻ ለመተያያና አለፍ ሲልም ለመገዳደያ ሰበብ ልናደርጋቸው አይገባም።
 
እንደቤተልሔሞቹ እንስሳት፣ መላእክትና ሰዎች በአንድነት ስንቆም ጠላት አይደፍረንም፤ አንዳችን ለአንዳችን ጥላ እንጂ ጠላት፣ ደጋፊ እንጂ አደናቃፊ፣ አቃፊ እንጂ ገፊ እንድንሆን ለህሊናችን አንፈቅድለትም፡፡ በአንድነት ስንቆም በተሰማራንበት መስክ ሁሉ ስኬታማና አሸናፊዎች እንሆናለን። ቀደምት አባቶቻችን አገራችንን ከጠላት በመጠበቁ ሂደት ያሳዩንም ይህንኑ ታላቅ ተግባር ነው።
 
ሌላው ከገና ወይም ከልደት ጋር ተያይዞ የምናስታውሰው ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› የሚለውን አባባል ነው፡፡ አባባሉ በገና ጨዋታ ጌትነትና ሎሌነት፣ ሀብትና ክብር፣ ሥልጣንና ዘር ምንም ቦታ አለመኖራቸውን ነው፡፡ በገና የጨዋታ ሜዳ ለመሳተፍ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡
 
የጨዋታ ሕጉም ሁሉንም በእኩልነት ያገለግላል፡፡ ይህ የጨዋታ ሕግ በሰዎች መካከል መተማመንን፣ መቻቻልን፣ አብሮነትን፣ እኩልነትን፣ አካታችነትን፣ አሳታፊነትንና ግለሰባዊ ነጻነትን ያጎናጽፋል። በአጠቃላይ የጨዋታ ሕጉ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል።
 
ከልደት ሌላው የምንማረው ሰላምንና ይቅርታን ነው። በክርስቶስ ልደት ለአለም ሁሉ የሚሆን ሰላም ተገኝቷል። በሰውና በፈጣሪ መካከል ከአምስት ሺህ አመታት በላይ የቆየው የጥል ግድግዳ በክርስቶስ መወለድ ተፈረካክሷል። ቀጭና ተቀጭ የነበሩት ሰውና መላእክትም አብረው ዘምረዋል።
 
አዳኝ እና ታዳኝ የሆኑት የዱር አራዊትና የቤት እንስሳትም በጋራ ሀሴት አድርገዋል። ለዘመናት ሲናፍቁት የነበረውን ሰላምንም በአብሮነት አጣጥመውታል።
 
ሰላም ከየትም የሚመጣ አይደለም። ሰላም የሚመጣው ጠላትን ከራስ ጋር በማስታረቅ ነው። ጠላቱን ከራሱ ጋር ያስታረቀ ሌሎችንም ለማስታቅ አይከብደውም። ከክርስቶስ ልደት የምንማረውም ይህንኑ ነው።
በልደቱ ይቅርታንም እንማራለን። አዳም በበደለው በዳዩ ይቅር ይበልኝ ሳይል ራሱ ፈጥኖ ይቅር አለው። ይቅር ማለት መውረድ ሳይሆን ከፍ ማለት ነው።
 
በመሆኑም የልደት በአልን ስናከብር በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል እላለሁ። በድጋሚ ለክርስቲያኖች በሙሉ መልካም በአል እንዲሆንላችሁ እመኛልሁ።
 
አገኘሁ ተሻገር
 
የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.