Fana: At a Speed of Life!

ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ የሚሲዮኖች ሚና ከፍተኛ ነው – አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪ የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ በሚደረገው ጥረት የሚሲዮኖች ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡
 
በሱሉልታ የአፍሪካ አመራር የልሕቀት ማዕከል ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ ሚሲዮን መሪዎች እና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የሚሰጠው ሥልጠና እንደቀጠለ ነው፡፡
 
በዛሬው መድረክ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዘርፍ አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡
 
በገለጻቸውም ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ዘረፉን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎችን እና የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አብራርተዋል፡፡
 
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከአሁን በፊት በመንግስት ቁጥጥር ስር ብቻ ተይዘው የነበሩ ዘርፎች ለግል ኩባንያዎች ክፍት መደረጋቸውን አንስተዋል።
 
ሚኒስትሩ የውጭ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ለመሳብ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን፣ያጋጠሙ ፈተናዎች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም ጠቅሰዋል።
 
በዚህ ወቅት ሚሲዮኖች በማምረቻው ዘርፍ ብቃት እና አቅም ያላቸው ኩባንያዎችን ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባቸው መጠቆማቸውን የሚኒስትሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ለኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ያሉ አቅሞችን እና ከመንግስት የቀረቡ ማበረታቻዎችንም በተገቢው ደረጃ ማድረስ ከሚሲዮኖች ይጠበቃል ብለዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.