Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በሁኔታዎች ተለዋዋጭነት የማይዋዥቅ መሆኑን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በሁኔታዎች ተለዋዋጭነት የማይዋዥቅ መሆኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ አስታወቁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለው ግንኙነት የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ መሆኑን ገልፀዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ስትራቴጂካዊ ትብብራዊ አጋርነት የተፈራረሙ መሆናቸውን ገልፀው ፥ ይህን ስምምነት ይበልጥ ወደ ተግባር ለመቀየር እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አቶ ደመቀ መኮንን ፥ የፖለቲካ ምክክር ማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት እና ከፊል የዕዳ ስረዛ ስምምነት መፈረሙንም አንስተዋል፡፡

ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ለማስቀጠልና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚረዳም ነው ያብራሩት።

አቶ ደመቀ በውይይታቸው ለሚኒስትር ቺን ጋንግ በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን እና ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገልፀዋል።

የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ በበኩላቸው ፥ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በሁኔታዎች ተለዋዋጭነት የማይዋዥቅ መሆኑን ገልፀዋል ።

“ዛሬ የተፈራረምነው የመግባቢያ ስምምነትም ይህን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ፥ በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና በዓለም አቀፍ መድረኮች ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.