Fana: At a Speed of Life!

በመሬት ጉዳይ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጉቦ ተቀብሏል በሚል የተከሰሰው የፋሲል አወቀ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በይዞታ ላይ እግድ ያለበትን ካርታ እንዲሰራ አደርጋለው በማለት ከባለ ጉዳይ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጉቦ ተቀብሏል ተብሎ የተከሰሰው ፋሲል አወቀ ያቀረበው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ።

ባለሙያው በአዲስ አበባ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር የሊዝ ውል ባለሙያ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ ያደረገው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ችሎቱ በተከሳሹ ላይ የቀረበው “ጉቦ መቀበል” የሚል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ነው፡፡

ክሱም ለተጠርጣሪው እንዲደርሰው የተደረገ ሲሆን፥ በንባብም ተሰምቷል።

ተከሳሹ የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ10(2) ስር የተመለከተውን መተላለፉን ዐቃቤ ኅግ ጠቅሷል፡፡

በክፍለ ከተማው የመሬት ልማት አስተዳደር የሊዝ ውል ባለሙያ ሆኖ ሲሰራም ነሃሴ 3 ቀን 2014 ዓ/ም የዓቃቤ ኅግ 1ኛ ምስክር የሆኑት ባለ ጉዳይ በይዞታቸው ላይ እግድ እንዳለ ካረጋገጠ በኋላ “ካርታ እንዲሰራሎት ከፈለጉ ገንዘብ ይክፈሉ” በማለት በቀዳሚነት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በስሙ በሚንቀሳቀስ የባንክ ሒሳብ ገቢ እንዲደረግለት አድርጓል ሲል ዐቃቤ ኅግ ከሷል፡፡

እንዲሁም ተጨማሪ 2 ሚሊየን ብር ያስፈልጋል በማለት እና በመጠየቅ በፈጸመው ጉቦ የመቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ዐቃቢ ኅግ ክስ መስርቶበታል።

ዐቃቤ ኅግ ያቀረበው ሁለተኛው ክስ ደግሞ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ኅጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሚል ነው፡፡

በዚህም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 /1/ ሀ ስር የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሹ ነሃሴ 06 ቀን 2014 ዓ/ም ገንዘቡን ማሲን ሮቤ ለተባለ ግለሰብ ያስተላለፈ መሆኑ ተጠቅሶ ክስ ተመስርቶበታል።

ተከሳሹ በበኩሉ ክሱ በችሎት ከተነበበለት በኋላ የዋስትና መብቱ እንዲከበር ጠይቋል።

የፍትኅ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቢ ኅግ በተከሳሹ ላይ የቀረበበት የሙስና ወንጀል ክስ አንቀጽ ዋስትና መብት ያስከለክላል ሲል የዋስትና ጥያቄውን በመቃወም ተከራክሯል።

ክርክሩን የተከታተለው ችሎቱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በነበረ ቀጠሮ የተከሳሹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

ተከሳሹ የክስ መቃወሚያ ካለው ለመጠባበቅ ለጥር 8 ቀን 2015 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.